በመቀሌ ለጀኔራል መኮንኖቹ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ዝግጅት ተጠናቋል - ኢዜአ አማርኛ
በመቀሌ ለጀኔራል መኮንኖቹ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ዝግጅት ተጠናቋል
መቀሌ ሰኔ 18 / 2011 የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና የሜጄር ጀኔራል ገዛኢ አበራ የቀብር ሥነሥርዓት አፈፃፀም ዝግጅት መጠናቀቁን የትግራይ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ። የቢሮ ኃላፊዋ ወይዘሮ ሊያ ካሳ እንደገለጹት የቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ''ሰማዕታት ቅሰኑ /እረፉ/፤ አንበረከክም!'' በሚል መሪ ቃል እንደሚከናወን አስታወቀዋል። ኃላፊዋ ወይዘሮ ሊያ ካሳ ዛሬ እንደገለጹት የጄኔራሎቹ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ለማከናወን አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንና የጄኔራሎቹ አስከሬን ዛሬ መቀሌ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ ሲደርስ አቀባበል ይደረግለታል። ነገ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ባለው ጊዜ በሰማዕታት ሐውልት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሽኝት ሥነ-ሥርዓትይካሄዳል። ጄኔራሎቹን በማስታወስ ዛሬ ከምሽቱ 11 ሰዓት በሁሉም የክልሉ ከተሞች የሻማ ማብራት ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን ወይዘሮ ሊያ አመልክተዋል። የጀኔራሎቹ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ነገ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በቅዱስ ገብርዔል ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም ገልጸዋል። ከቀብር መልስ ለጄኔራል መኮንኖቹ ቤተሰቦች በሰማዕታት ቅጥር ግቢ ውስጥ የማፅናናት መርሐ ግብር እንደሚካሄድ አስረድተዋል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመቀሌ ከተማን ጨምሮ ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተውጣጡ የሕዝብ ተወካዮችና የትግል ጓዶቻቸው እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል። ጄኔራል መኮንኖቹ ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ላይ በጀኔራል ሰዓረ ጠባቂ በተተኮሰ ጥይት መገደላቸው ይታወሳል።