የማዕከላዊ ጎንደር ሕዝብና የጸጥታ ኃይል ተጠርጣሪዎች ዞኑን መሸሸጊያ እንዳያደርጉት እየሰራ ነው-- ዋና አስተዳዳሪው - ኢዜአ አማርኛ
የማዕከላዊ ጎንደር ሕዝብና የጸጥታ ኃይል ተጠርጣሪዎች ዞኑን መሸሸጊያ እንዳያደርጉት እየሰራ ነው-- ዋና አስተዳዳሪው
ጎንደር ሰኔ 17/2011 የማዕከላዊ ጎንደር ሕዝብና የጸጥታ ኃይል በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ግድያ ተጠርጣሪዎች ዞኑን መሸሸጊያ እንዳያደርጉት በመሰራት ላይ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው አስታወቁ። ዋና አስተዳዳሪው አቶ ብርሃኑ ጣዕምያለው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስረዱት ሕዝቡና የፀጥታ ኃይሉ በባህር ዳር ከተማ ጥፋት አድርሰው ለመሸሽ የሚሞክሩ ተፈላጊዎችን ተከታትሎ ለሕግ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል። የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት በማስጠበቅ የተጀመረው ሕዝባዊ ለውጥ ለማስቀጠል አመራሩና የፀጥታ ኃይሉ ግዳጁን ለመወጣት ከሕዝቡ ጋር እየሰራመሆኑን ተናግረዋል። ዞኑን ለመበጥበጥና ለማተራመስ የሚጥሩ ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍም በዞኑ ከጸጥታ ኃይሉ የተውጣጣ ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት መቋቋሙን ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል። መስዕዋትነት የከፈሉት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ዞኑን ከግጭት ቀጠናነት በማውጣት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ሲጥሩ የነበሩ ''ውድ የሕዝብ ልጆች'' ሲሉም ገልጸዋቸዋል። የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በስብሰባ ላይ ሆነው የተገደሉት ባለፈው ቅዳሜ ነበር።