የደቡብ ወሎ ዞን፣ የደሴ ከተማ አስተዳደርና የሰሜን እዝ ጠቅላይ መምሪያ በተፈጸመው ጥቃት ማዘናቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ወሎ ዞን፣ የደሴ ከተማ አስተዳደርና የሰሜን እዝ ጠቅላይ መምሪያ በተፈጸመው ጥቃት ማዘናቸውን ገለጹ
ሰኔ 17/2011 የደቡብ ወሎ ዞን እና የደሴ ከተማ አስተዳደሮች በክልሉ በተፈጸመው ጥቃት በጠፋው የሰው ሕይወት ማዘናቸውን ገለጹ። በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ጠቅላይ መምሪያም በአዲስ አበባና በባህር ዳር ከተሞች በደረሰው ጥቃት የሰው ሕይወት በማለፉ ጥልቅ ሀዘንእንደተሰማው አስታውቋል። የደቡብ ወሎ ዞን፣ የደሴ ከተማ አስተዳደርና የሰሜን እዝ ጠቅላይ መምሪያ በክልሉ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ በተደረገው ሙከራ የተፈጸመውንጥቃትንም አውግዘዋል። የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አቶ እሸቱ የሱፍ እንዳሉት በሕዝብ ትግል የመጣውን ለውጥ በማስቀጠል የሕብረተሰቡን ጥቅም ለማስከበር ከተለያዩአካላት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው። ሕብረተሰቡ በየትኛውም አካባቢ ያለ ስጋት ሰርቶ እንዲኖርና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን በትኩረት እየተሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት ይህ ጥቃት ተፈጽሞየክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መሰዋታቸው እንዳሳዘናቸውና ድርጊቱንም እንደሚያወግዙት ተናግረዋል። “ሕዝቡ በእዚህ ሳይደናገጥና የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ለውጡን ማስቀጠል ይኖርበታል” ብለዋል። ለሕዝብ ሲሉ ለተሰው አመራሮች ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን ተመኝተዋል። በተመሳሳይ ዜና የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶክተር መለሰ መኳንት የተፈፀመው ጥቃት የአማራ ሕዝብን የማይመጥን፣ አሳፋሪና ኢሰብአዊ ድርጊትመሆኑን ገልፀዋል። “የኢትዮጵያ አንድነትና የህዝቡን አብሮነት በማስቀጠል የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ እየተሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት ይህ መራር ሀዘንቢገጥመንም ከዓላማችን አንደናቀፍም” ብለዋል። ከአጎራባች ክልሎች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች ጋር በመቀናጀት የህዝቡን ሰላም በማስጠበቅ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል እንደሚሰራም ተናግረዋል። “በብሔርና በሃይማኖት በመከፋፈል ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚሞክሩ የፖለቲካ ጥቅመኞችንም ከህብረተሰቡ ጋር እንታገላለን” ብለዋል ከንቲባዶክተር መለሰ። መገናኛ ብዙሀን፣ ወጣቱ፣ የሀገር ሸማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች አገር የጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡም ጠይቀዋል። በጥቃቱ ሕይወታቸው ላለፈ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከተማ አስተዳደሩ ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማውና ድርጊቱን እንደሚያወግዝ በመግለጽለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል። በተመሳሳይ የኢፌድሪ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም በነበሩት ጀነራል ሰዓረ መኮንን ፣ በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንንና የሥራባልደረቦቻቸው ላይ በደረሰው ጥቃት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል። ጠቅላይ መምሪያው ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ የሰሜን እዝ መስራች በነበሩ ክቡር ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ሜጄር ጀነራል ገዛኢአበራ እንዲሁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶርክተር አምባቸው መኮንን እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ላይ በደረሰው ድንገተኛ ጥቃት ጥልቅ ሀዘንእንደተሰማው አስታውቋል። ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን የህዝባዊ ባህሪ ተምሳሌትነት አዲስ ምዕራፍን እያንጸባረቁ ባሉበት ጊዜ የደረሰባቸው ጥቃት የሰራዊቱን ህብረብሔራዊ ውበት ለማደብዘዝ የተደረገ ሴራ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል። የሀገሪቱን አንድነት ለመበታተን ሌት ተቀን በማይተኙ ኃይሎች አማካኝነትና በተቀነባበረ የቅጥረኞች ሴራ የተፈፀመ ግድያ መሆኑንም መምሪያውአስታውቋል። የሠራዊቱን አንድነት ለመሸርሸር በሚጥሩ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ሠራዊቱ ምን ግዜም ዝግጁ መሆኑንም የሰሜን እዝ ጠቅላይመምሪያ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ጀነራል ሰዓረ አንድ ሆነን እንድ ሺህ፣ ሺህ ሆነን እንደ አንድ እንሰለጥናለን፣ እንዘጋጃለን፣ እንዋጋለን፣ እናሸንፋለን የሚል የህዳሴ መስመር በማንገብበታላላቅ ድሎች የታጀቡ መሪ እንደነበሩም መግለጫው አመልክቷል። “ሠራዊቱ በዓላማው ጸንቶ በማንም ሳይረታ የሰላም፣ የልማትና የድል ኃይል ሆኖ ይዘልቃል” ብለዋል። የሰሜን እዝ ጠቅላይ መምሪያ በደረሰው ድንገተኛ ጥቃት ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች፣ ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና ለኢፌድሪ መከላከያሠራዊት አባላት መጽናናትን ተመኝቷል።