ቀጥታ፡

ጋህአዴን ጎሰንተኝነትና የብሔርተኝነት እንደሚታገል አስታወቀ

ጋምቤላ ሰኔ 17/2011 የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህአዴን) ጎሰንተኝነትና የብሔርተኝነት አመለካከቶችን በመታገል ለክልሉ ሰላምና ልማት በትኩረት እንደሚሰሩ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ ። ከፍተኛ አመራሮቹ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በወታደራዊ መኮንኖች ላይ የተፈፀመውን እኩይ ድርጊት አጥብቀው አውግዘዋል። የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ለአራት ቀናት ያካሄዱትን ስልጠና ሲያጠናቅቁ ባወጡት የአቋም መግለጫ እንዳረጋገጡት የጎሰኝነት ፣ የጠባብነትና የብሔርተኝነትን አመለካከቶችን በመታገል ሰላምና ልማት ለማስፈን ይሰራሉ። በተለይም ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር በተለይም የሥራ አጥነት ችግርን ለመፍታት እንደሚሰሩም ገልጸዋል። በክልሉ የተጀመረውን ለውጥ በማስቀጠልና ችግሮችን በማረም ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት ትኩረት እንደሚሰጡም አስታውቀዋል። የክልሉን የተፈጥሮ ሃብት ወደ ልማት በማዋል የወጣቱን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ በገቢ አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ልማትን ለማፋጠን እንደሚሰሩም ገልጸዋል። የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ትኩረት እንደሚሰጥም  በመግለጫው ተመልክቷል። ድርጅቱ የአደረጃጀትና የአሰራር መመሪያዎችን ወቅቱ ባገናዘበ መልኩ ለማከናወን እየሰራ መሆኑንም ገልጿል። ተሳታፊዎቹ በአማራ ብሐራዊ ክልላዊ መንግሥትና ከፍተኛ አመራሮችና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ላይ የተፈፀመውን እኩይ ድርጊት አጥብቀው እንደሚያወግዙም ገልጸዋል። ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብም መጽናናትን ተመኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም