አማራ ክልል የገጠመውን ችግር ለመፍታት ሁሉም ህብረተሰብ ከክልሉ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
አማራ ክልል የገጠመውን ችግር ለመፍታት ሁሉም ህብረተሰብ ከክልሉ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ

ሰኔ 16/2011 የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የገጠመው ችግር የኢትዮዽያና የህዝቦቿ ችግር መሆኑን ተገንዝቦ ሁሉም ህብረተሰብ ከክልሉ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀረበ። ክልሉ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ክልሉ የገጠመው ችግር የአገራችን ኢትዮጵያና የህዝቦቻችን ችግር ነው። ''በዚህ ወቅት ከጎናችን በመሆን ክልላችንን ለማረጋጋት በምናደርገው እንቅስቃሴ አብራችሁን ለሰላም በጋራ እንድትቆሙ'' ሲል ጥሪውን አስተላልፋል። ክልሉ የገጠመውን ጊዜያዊ አደጋ ለመመከት የክልሉና የፌዴራል መንግስት በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ የፀጥታ መዋቅሩ ከምንግዜውም በላይ በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ እንደሆነ ጠቁሟል። ሙሉ የመግለጫ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡- ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግለጫ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ህዝቦች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞችና ፍላጎቶች ለማረጋገጥ፣ የህዝቡን የለውጥ ተስፋ በማለምለም ፍሬያማ እንዲሆን ለማድረግ ከክልሉና ከሌሎች ክልሎች ጋር በመተባበር በስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ይታወቃል። የክልሉ መንግስት የህዝቡን የለውጥ ፍላጎቶች ለማሳካትና እንደ ክልልም ሆነ እንደ አገር ጥቅሞቻችንን ለማስጠበቅ እያደረጋቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች የተለያዩ ፈተናዎችና መሰናክሎች ቢገጥሙትም ፈተናዎቹንም ሆነ መሰናክሎቹን የተለያዩ አመለካከቶች ሳይገድቡን ከህዝባችን ጋር ሆነን በጥበብ እያለፍናቸው የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት ፈፅሞ ወደማይቀለበስበት ደረጃ እንዲሸጋገር መሰረት እየጣለም ይገኛል። በተለይ በቅርቡ ከክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮችና የክልላችን ምሁራን ጋር ባደረግነው ውይይት፣ የህብረተሰቡ ተወካዮችአበክረው ሲያነሷቸው የነበሩ የህግ የበላይነትና የፀጥታ ችግሮች በክልሉ የሰላምና የልማት ጥያቄ ዋነኛ ማነቆ እየሆኑ መምጣታቸውን በመግለፅ ችግሩን ለመፍታት ህዝባችን ከክልሉ መንግስት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ለመስራት ቁርጠኛ አቋም ማሳለፉ ይታወቃል። በትናንትናው እለትም የክልላችን ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ዶክተር አምባቸው መኮንን እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ክቡር አቶ እዘዝ ዋሴ በብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ በተቀነባበረ ሴራ ስምሪት በተሰጣቸው የመፈንቅለ መንግስት አድራጊ ቡድኖች በተሰነዘረባቸው ጥቃት ተሰውተዋል። አመራሮቻችን በአጥቂዎቹ በተሰነዘረ ጥቃት የተሰዉት የህዝቡን አደራና የለውጥ ፍላጎትና ጥያቄዎች ለመመለስ ከሌሎች አመራሮች ጋር በቢሮአቸው በተሰበሰቡበት ወቅት ነበር። የክልላችን ርዕሰ መስተዳድር ክቡር ዶክተር አምባቸው መኮንን እና የርዕሰ መስተዳድሩ የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ ክቡር አቶ እዘዝ ዋሴ በመፈንቅለ መንግስት ሴረኞቹ በደረሰባቸው ጥቃት በመሰዋታቸው የክልላችን መንግስት ጥልቅ ሀዘን የተሰማው መሆኑን ይገልፃል። አጥፊዎቹንም ለህግ ለማቅረብ ከፌዴራል የፀጥታ መዋቅሩ ጋር እየሰራ ይገኛል። መላው የክልላችን ህዝቦች፣ የአማራ ክልል ህዝቦች በተለይ በቅርቡ ያነሳችኋቸው የልማት፣ የሰላምና የህግ የበላይነት ይጠበቅልን ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ የሚያሻቸው ናቸው። የክልሉ መንግስትና መስዋዕትነት የከፈሉት ክቡር ጓዶቻችንም ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በተጨባጭ እየተንቀሳቀሱ በነበረበት ወቅት ነው። በብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ የተመራው የመፈንቅለ መንግስት አድራጊ ሴረኛ ቡድንም የህዝቡን ፍላጎት ተፃርሮና ህዝቡ የሰጠውን አደራ ወደ ጎን ብሎ ክህደት ፈፅሟል። ክልላችንን ወደ ተረጋጋ ሰላም ለመመለስ ጥረት በምናደርግበት፣ የከተሞቻችንን ሰላም ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በተለየ እየተንቀሳቀስን ባለንበትና አርሶ አደሮቻችን በአፍላ የአዝመራ ወቅት ላይ በሚገኙበት በዚህ ወቅት የተፈፀመው ይህ ጥቃት በመላው የአማራ ክልል ህዝቦች ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው። መላው የክልላችን ህዝብም ሀይማኖት፣ ብሄር፣ እድሜ፣ ሀብት እና ሌሎች ልዩነቶች ሳያግዱት አንድ ሆኖ በመቆም ይህን ጊዜያዊ ችግር ማለፍ የሚገባው ወቅት ላይ ይገኛል። በመሆኑም የተከበርከው ህዝባችን፣ ክልላችን የገጠመውን ይህንን ጊዜያዊ አደጋ ለመመከት የክልላችንና የፌዴራል መንግስት በቅንጅት እየሰሩ ሲሆን የፀጥታ መዋቅሩም ከምንግዜውም በላይ በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን። ይህንን በመገንዘብ ክልሉን በማረጋጋት፣ ሰላሙን በማስጠበቅ ህዝባችን ከጎናችን እንድትቆም በአክብሮት እንጠይቃለን። መላው የሀገራችን ህዝቦች፣ ክልላችን የገጠመው ችግር የአገራችን ኢትዮዽያና የህዝቦቻችን ችግር ነው። በመሆኑም በዚህ ወቅት ከጎናችን በመሆን ክልላችንን ለማረጋጋት በምናደርገው እንቅስቃሴ አብራችሁን ለሰላም በጋራ እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።