በአማራ ክልል የተፈፀመው ጥቃትና መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ፋሽስታዊ ነው ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የተፈፀመው ጥቃትና መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ፋሽስታዊ ነው ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ
ሰኔ 16/2011 በአማራ ክልል ትናንት የተፈጸመው ጥቃትና የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ፋሽስታዊና ኢ-ህግ መንግስታዊ ተግባር ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ። አቶ ሽመልስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንንና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ እንደዚሁም በኢፌድሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል። የራሳቸውንና የቡድን ጥቅም በህዝብ ላይ ለመጫን በሚሹ አካላት በአማራ ህዝብ ላይ የተሰነዘረው ይህ ጥቃት በአሮሞ ህዝብና መንግስት ላይም እንደተፈጸመ ይቆጠራል ብለዋል። ተግባሩየተጀመረውንና ከአገሪቱ ዜጎች ባሻገር በመላው አለም እውቅና የተቸረውን የለውጥ ሂደት ማደናቀፍን ያለመ መሆኑንም አመልክተዋል። ለኢትዮጰያ ህዝቦች እኩልነትና ነጻነት እራሳቸውን የሰዉ አመራሮች በአገሪቱ በተገኘው ለውጥ ውሰጥ የማይተካ ሚና ነበራቸው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የተገኘው ለውጥ ለማደናቀፍ የተጀመረው ይህ የጥፋት ዓላማ ከስሯል፤ የተጀመረው የለውጥ ጎዳና በምንም መንገድ በማንም ኃይል ሊደናቀፍ አይችልም፤ የሚከፈለው መስዋእትነት ሁሉ እየተከፈለ ግቡን እንዲመታ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል። ተግባሩ መላው የአገሪቱ ህዝብን ለበለጠ ትግልና ትጋት የሚያነሳሳው እንጂ በቀላሉ ለሽንፈት የሚዳርገው እንደማይሆንም ጠቅሰዋል። የክልላዊ መንግሰትም የአማራ ህዝብ የህግ የበላይነትን ለማጠናከር በሚሰራው ስራ ሁሉ የክልሉ መንግስት ከጎኑ መሆኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል። "የእነዚህ ኢትዮጵያን ህልፈት ለእኩልነት፣ ነጻነትና ወንድማማች እውን መሆን ተብሎ የተከፈለ መስዋእትነት ነው" በማለትም አቶ ሽመልስ ገልፀዋል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በደረሰው ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው የተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንንና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ ከክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር ትናንት ስብሰባ ላይ ባሉበት በጀኔራል አሳምነው ጽጌ በተመራ ሃይል በደረሰባቸው ጥቃት ነው ህይወታቸው ያለፈው። በተጨማሪ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ በጥቃቱ በደረሰባቸው ጉዳት ህክምና እንዲከታተሉ እየተደረገ ይገኛል። አመራር አባሎቹ ላይ ጥቃት የፈጸሙት አብዛኞቹ በቁጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ የክልሉ የጸጥታ ሃይሎች ቀሪዎቹን ለመያዝ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን መንግስት አስታውቋል። የኢፌድሪ መከላከያ ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ም ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በጠባቂያቸው በተፈፀመባቸው የተቀነባበረ ጥቃት ህይወታቸው አልፏል።