ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት የአገሪቱንና ህዝቦቿን ደህንነት ለማረጋገጥ በሚያስችል ጠንካራ ቁመና ላይ ናቸው -የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሰኔ 16/2011 የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን አንድነትና የህዝቦቿን ሰላም ለማረጋገጥ በሚያስችል ጠንካራ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንንና የአገልግሎት ጊዜያቸውን ጨርሰው በጡረታ በተሰናበቱት ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ህልፈት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል። የመከላከያ ሰራዊት የመረጃ ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ሀሰን ኢብራሂም በጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ህልፈት እንደዚሁም በአማራ ክልል የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። ''ጥቃቱ በግለሰቦች ላይ የተፈጸመ ተራ አደጋ ሳይሆን የኢትዮጵያን የቆየ አንድነት በማደፍረስ፣ በአገር ላይ የመፍረስ አደጋ መፍጠር፣ መንግስትን ማዳከምና በአጋጣሚውም የግል ዓላማቸውን ለማሳካት የተፈጸመ ተግባር ነው'' ሲሉ ገልፀዋል። በተለይም በሰራዊቱ መካከል የብሄር  ግጭት መፍጠርና   ሰላምን  የማደፍረስ   ተልዕኮ  እንደነበረው ሌተናል ጀነራሉ ጠቁመዋል። ''ይህም የሰራዊቱን ተጨባጭ እውነታ ካለመገንዘብ የመነጨ በጊዜያዊ ጥቅም በመስከር የተፈጸመና የከሰረ ሀሳብ ነው'' ብለዋል። በተለይም ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ጊዜ ወዲህ ሰራዊቱ ከብሄር ይልቅ ለአገሪቱና ህዝቦቿ አንድነት እንዲቆም የሚያስችል ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል። የመከላከያ ሰራዊቱ በተለያየ ጊዜ የሚገጥመውን ችግር በራሱ እየፈታ የመጣና በዚህ ረገድ ብዙ ልምድ ያለው መሆኑን የገለጹት ሌተናል ጀነራል ሀሰን በአሁኑ ወቅት በሰራዊቱ ውስጥ ምንም የሚያሰጋ ጉዳይ አለመኖሩን አረጋግጠዋል። በአሁኑ ወቅት ሰራዊቱ በከፍተኛ አመራር አባላቱ ህልፈት በእጅጉ ያዘነ ቢሆንም በውስጡ ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ፍጹም የተረጋጋ፤ ጽናቱንና አንድነቱን አጠናክሮ ጠላቶቹን ለማሳፈር የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሆነም አስታውቀዋል። ''የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለአገርና ህዝብ አንድነት የቆመ መሆኑን ያመለከቱት ኃላፊው የተሻለችና የበለፀገች ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደቱ የበኩሉን ሚና አጠናክሮ ይቀጥላል'' ብለዋል። በሰራዊቱ ከፍተኛ አመራር አባላት ሞት ለመላው የሰራዊቱ አባላትና ለኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን ተመኝተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም