ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዙ - ኢዜአ አማርኛ
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዙ
አዲስ አበባ ሰኔ 16/2011 አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ህዝቡ አገሪቷ ያጋጠማትን ችግር በትዕግስት እንዲያልፍ መንግስት የማረጋጋት ስራ እንዲሰራ ጠይቀዋል። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ''መንግስት አገሪቷ ያጋጠማትን ፈተና ከዚህ የባሰ ችግር እንዳያስከትል ህዝቡን የማረጋጋት ስራ መስራት አለበት'' ብለዋል። ሁሉም ዜጋ ለሰላሙ ዘብ ካልቆመ አሁን የተፈጠረው ችግር በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች እንደማይፈጠር ዋስትና እንደማይኖረው አስገንዝበው፤ በስሜታዊነት ወዳልተፈለገ ግጭት ማምራት የበለጠ ችግር ውስጥ የሚከት በመሆኑ ህዝቡ አሁን ያለው ሁኔታ እስኪያልፍ በትዕግስት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ሰብሳቢ አቶ ተሻለ ሰብሮ ''የአገር ምሰሶ በነበሩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ላይ የደረሰው ጥቃት ልብ የሚነካ ነው'' ብለዋል። መንግስት ህዝብን በማረጋጋት ችግሩን በፈጠሩ ሃይሎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የኢትዮጰያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ በበኩሉ በሃይል እርምጃ የዜጎችን ህይወት መቅጠፍና የህዝብን ሰላም ማናጋት ኢ-ዴሞክራሲያዊ ተግባር መሆኑን አስታውቋል። ለህዝብ ወገንተኛና ለሰላም ዘብ ሊቆም የሚገባውን የታጠቀ ሃይል እኩይ ተግባር መፈጸሙ ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በቁርጠኝነት ሊታገለው እንደሚገባም ነው ፓርቲው ያስገነዘበው። የራስን የፖለቲካ ፍላጎት በሃይል ለማሳካት የሚደረግ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመምጣቱ በቸልታ ሊታለፍ እንደማይገባም አሳስቧል። ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለም ውሎ አድሮ የአገሪቷን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እንዲሁም የህዝቡን ተከባብሮ የመኖር እሴት የሚፈታተን መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል ብሏል። በአማራ ክልልና በፌዴራል መንግስት የተፈጸመው የሃይል ጥቃት ህዝቡ በማውገዝ ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም የፓርቲዎቹ አመራሮች ለደጋፊዎቻቸውና ለአባላቶቻቸው ጥሪ አቅርበዋል። የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ህይወታቸውን ላጡ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው፣ ለቤተሰቦቻቸና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ተመኝተዋል።