ክልሎቹ በዶክተር አምባቸው መኮንን፣ በጀነራል ሰዓረ መኮንንና በሌሎች አመራሮች ህልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ክልሎቹ በዶክተር አምባቸው መኮንን፣ በጀነራል ሰዓረ መኮንንና በሌሎች አመራሮች ህልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ
ሰኔ 16/2011 በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና በሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ላይ በተቃጣ ጥቃት በደረሰው ህልፈተ ሕይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን የሐረሪ፣ የአፋርና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስታትና የድሬዳዋ አስተዳደር ገለጹ። የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ለህልፈተ ሕይወት የተዳረጉት ከፍተኛ አመራር ለሀገሪቱ የላቀ አገልግሎት የሰጡ ናቸው። በአመራርነት ዘመናቸው በቅንነትና በታማኝነት አገራቸውን ያገለገሉ መሪዎች እንደነበሩም ጠቅሷል። አመራሮቹ አስከ ህልፈተ ሕይወታቸው ድረስ በክልሉ የተለያዩ ዘርፎችና በሀገር ደረጃ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረከቱ መሆናቸው የገለጸው የክልሉ መንግስት መግለጫ፣ በተፈጸመው ድርጊት በእጅጉ ማዘኑንና ድርጊቱንም እንደሚያውግዝ አስታውቋል። በሕይወት ላጣናቸው ለሀገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች ሞት የክልሉ መንግስት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገልጾ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል። በተመሳሳይ ዜና በአማራ ክልላዊ መንስግትና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የተፈፀመውን ግድያ የአፋር ክልላዊ መንግስት አውግዟል። የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ከሎይታ በትናንትናው ዕለት በአማራ ክልል ርዕስ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንንና የርዕሰ መስተዳድሩ የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ ላይ በተፈፀመው ግድያ በክልል መንግስትና ህዝብ ስም የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል። ግድያው የክልሉ መንግስት ለህዝቦች የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የጀመረውን ሁለተናዊ ለውጥ ፈጽሞ እንደማያደናቅፈውም አቶ አህመድ ተናግረዋል። የአፋር ክልላዊ መንግስትና ህዝብ ግድያውን እንደሚያወግዝ ገልጸው፣ “የክልሉ መንግስት ከአማራ ክልልና ህዝብ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው” ብለዋል። በክልሉ መንግስት ላይ የተሞከረውን መፈንቀለ መንግስት በማክሸፍ ተልዕኮ ላይ በነበሩ ጀኔራል ሰዓረ መኮንን እንዲሁም ከእሳቸው ጋር በነበሩና በቅርቡ በጡረታ በተገለሉት ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ሞት የክልሉ መንግስት የተሰማውን ሀዘን ገልጸዋል። አመራሮቹ የከፈሉት መስዋዕትነት ለህዝባዊ ወገንተኝነትና ለሀገር ያላቸውን ወዳጅነት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም አቶ አህመድ ተናግረዋል። በሌላ በኩል በአማራ ክልል ርዕስ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን ላይ የተፈፀመውን ግድያ አጥብቆ እንደሚያወግዝ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት አስታውቋል። የክልሉ መንግስት ዛሬ በሰጠው መግለጫ በአማራ ክልል ርዕስ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን ላይ የተፈፀመውን ግድያ አጥብቆ በመቃወም ድርጊቱን አውግዟል። "በክልሉ መንግስት ላይ የተፈፀመው የመፈንቀለ መንግስት ሙከራ ህገመንግስቱን በኃይል ለመናድ የተደረገ በመሆኑ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት በምንም መልኩ አይቀበለውም" ብሏል በመግለጫው። ሀገሪቱ በለውጥ ጎዳና በምትጓዝበት በአሁኑ ወቅት ህጋዊነት በሌለው አግባብ ስልጣንን ለመቆጣጠር ሙከራ ማድረግ የዜጎችን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚጥስ ስርአት አልበኝነት አካሄድ አንድ ማሳያ ነው ሲልም ተጠቅሷል። ከለውጡ በተጻራሪ የቆሙ ጥቂት ኃይሎች ሙከራ ብዙሃኑን እንደማይወክል የገለጸው መግለጫው መላው የሀገሪቱ ህዝብ ከለውጡ ጎን በመቆም የለውጡን ተስፋ ማስቀጠል እዳንለበት ጥሪ አቀርቧል። የድሬዳዋ አስተዳደርም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል። አስተዳደሩ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው በፀረ ለውጥ ኃይሎች በተካሄደው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የሕይወት መስዋዕትነት በከፈሉት ዶክተር አምባቸው መኮንን ግድያ እጅጉን አዝኗል። “የድሬዳዋ አስተዳደር ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛል” ብሏል በመግለጫው። የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ዶክተር አምባቸው መኮንን በሀገር ደረጃ ለተመዘገበው ለውጥ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱና በህዝቡ ዘንድ ታላቅ ፍቅርና ተቀባይነት ያተረፉ መሪ እንደነበሩም መግለጫው አትቷል። በመፈንቅል መንግስት ሙከራው ሀገራዊ ለውጡ እንደማይደናቀፍና መላው ህዝብም መስዋዕትነት የተከፈለበትን ለውጥ ከዳር ሊያደርሰው እንደሚገባ በመግለጫው ተመልክታል።