ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአማራ ክልል አመራሮችና በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም በደረሰው የህይወት መስዋዕትነት የተሰማትን ሃዘን ገለጸች

ሰኔ16/2011 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአማራ ክልል አመራሮችና በመከላከያ አመራር ላይ በደረሰው የህይወት መስዋዕትነት የተሰማትን ጥልቅ ሃዘን ገለጸች። ትናንት አመሻሽ ላይ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ላይ በነበሩበት ወቅት በክልሉ የጸጥታ ሃላፊ ጀኔራል አሳምነው ጽጌ አቀነባባሪነት በተደረገ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮነን እና የአደረጃጀት አማካሪ እዘዝ ዋሴ ተሰውተዋል። ይህ ከሆነ ከአንድ ሰዓት በኋላ ችግሩን ለመፍታት እየሰሩ የነበሩት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን እንዲሁም የአገልግሎት ጊዜያቸውን አጠናቀው በጡረታ የተገለሉት ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ የህይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል። በተጨማሪ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ በጥቃቱ በደረሰባቸው ጉዳት ህክምና እንዲከታተሉ እየተደረገ ይገኛል። በሌላ በኩል በኢፌዴሪ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ሳዕረ መኮንን እና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ላይ በተፈጸመው ግድያም ቤተክስርቲያኗ  የተሰማትን ጥልቅ ሃዘን ገልጻለች። በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተከሰተው ድንገተኛ አደጋ ሳይደናገጥና ሳይከፋፈል አንድነቱንና ሰላሙን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስባለች። ህዝቡም አሁን ላይ በአገሪቱ የተጋረጠውን ፈተናም በትዕግስትና በጸሎት እንዲጠብቅም ቤተክርስቲያኗ ጥሪ አስተላልፋለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም