የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደርና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪያቸው ተሰው - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደርና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪያቸው ተሰው
ሰኔ16/2011የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንንና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪያቸው ትናንት በተፈጸመ ጥቃት ተሰውተዋል። የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ትናንት በተፈጸመው የመፈንቅ ለመንግስት ሙከራ ርዕሰ መስተዳደሩ ዶክተር አምባቸው መኮንንና የአደረጃጀት ዘርፍ አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ ከክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር ስብሰባ ላይ በነበሩበት ወቅት የክልሉ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ በነበረው ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በተቀነባበረ ሴራ በደረሰባቸው ጥቃት ተሰውተዋል። ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ አዲሱ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በምህረት ከተለቀቁት አንዱ ናቸው። በክልሉ የተጀመረውን ለውጥ ለማፋጠን ሚና እንደሚኖረው ታምኖ በቢሮ ኃላፊነት መሾሙ ይተወሳል። በዚሁ በተቀነባበረ ሴራ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ በተፈጸመባቸው ጥቃት ጉዳት ስለደረሰባቸው ህክምና እንዲከታተሉ እየተደረገ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ፤ በአማራ ክልል ባህር ዳር ላይ የተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መዋሉን አረጋግጠዋል። ድርጊቱ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅትም ጥቃት የፈጸሙት አብዛኞቹ መያዛቸውን ነው የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ የተመለከተው። የክልሉ የጸጥታ ኃይል ቀሪዎቹን ጥቃት ፈጻሚዎች ለመያዝ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ትናንት ማምሻውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሬታርያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለኢቲቪ በሰጡት መግለጫ ጥቃቱ በተደራጀ መልኩ የተከናወነ ነው። ትናንት በ11:00 ሰዓት ላይ የተፈጸመው ይሄ ጥቃት ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ያለመ ስለመሆኑ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተናገሩት። ክልሉ እየተረጋጋና የህዝቡን የህግ የበላይነት ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ ባለበት ወቅት የተሰነዘረው ጥቃት የክልሉ መንግስት ብቻ ሳይሆን የክልሉ ህዝብ ላይ የተሞከረ መሆኑ ተጠቁሟል። አቶ ንጉስ እንደገለጹት፤ ጸረ-ህገ መንግስትና የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንዲሁም በታጠቁ ኃይሎች የሚደረጉ እቅስቃሴዎች ተቀባይነት የላቸውም። ክልሉን ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በትብብር እንዲሰራ ጥሪ ያቀረቡትም በዚሁ ወቅት ነው። በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ላቀ አያሌውና በሌሎች አመራር እየሰጡ መሆኑ ተጠቁሟል።