በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደረገ

88
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2011በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉን በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬተሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ። አቶ ንጉሱ ማምሻውን ለኢቲቪ በሰጡት መግለጫ በክልሉ መንግስት ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጓል። በተደራጀ ሁኔታ በመንግስት መዋቅር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የተሞከረው የተደራጀ እንቅስቃሴ ከሽፏል ነው ያሉት አቶ ንጉሱ። ክልሉ ወደ መረጋጋት እየመጣ ባለበትና ህዝቡ ቀደም ሲል ያነሳ የነበረውን የህግ የበላይነት ጥያቄ ለመመለስ እየተሰራ ባለበት ወቅት የተሰነዘረው ጥቃት የክልሉ መንግስት ብቻ ሳይሆን የአማራ ህዝብ ላይ የተሞከረ ነው ብለዋል። ሙከራው ክልሉን ለማተራመስና የህዝቡን ህልውና አደጋላይ ለመጣል ያለመ መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግስት ሁኔታውን የማስተካከልና ክልሉን የማረጋጋት ትዕዛዝ እንደተሰጠው ገልጸዋል። የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ በመግባት ይህን መሰሉን ተግባር የመግታት ስራ እንደሚሰራና ህብረተሰቡም አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ መልዕክት አስተላልፈዋል። ጸረ ህገመንግስትና መፈንቅለ መንግስቶች እንዲሁም በታጠቁ ኃይሎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ገልጸው ክልሉን ወደነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም