ስድስተኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነገ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ስድስተኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነገ ይካሄዳል
አዲስ አበባ ሰኔ 2/2010 የ2018 ስድስተኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነገ በስዊድን ርዕሰ መዲና ስቶክሆልም ይካሄዳል። የመጀመሪያዎቹ አምስት ውድድሮች በኳታር ዶሃ፣ በቻይና ሻንጋይ፣ በአሜሪካ ኢውጂን፣ በኢጣልያ ሮም እና በኖርዌይ ኦስሎ ተካሂደዋል። ነገ በስቶክሆልም ባውሀውስ ጋላን ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት በሚካሄደው ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች በሚካሄዱ ውድድሮች ይሳተፋሉ። በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች አትሌት ሃብታም ዓለሙ፣ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይና አትሌት በሱ ሳዶ ይሳተፋሉ። አትሌት ሀብታም ከትናንት በስቲያ በኦስሎ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ በ800 ሜትር የሴቶች ውድድር ሶስተኛ መውጣቷ የሚታወስ ነው። የዘንድሮው ውድድር በኳታር ዶሃ ሲጀመር በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች አትሌት ሀብታም ዓለሙ ሶስተኛ፣ አትሌት በሱ ሳዶ አራተኛና አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ስድስተኛ መውጣታቸው ይታወቃል። አትሌት ሀብታም በ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር ስድስት የዳይመንድ ሊግ ነጥብ አላት። አትሌት ጫልቱ ሚያዚያ 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው 47ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ800 ሜትር ሴቶች ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወሳል። በአምስት ሺህ ሜትር ወንዶች አትሌት ሰለሞን ባረጋና አትሌት አባዲ ሀዲስ የሚሳተፉ ሲሆን በ800 ሜትር ወንዶች አትሌት ቶሎሳ ቦደና ይወዳደራል። የባውሀውስ ጋላን ስታዲየም በ31 የተለያዩ ርቀቶች የሚካሄዱ ውድድሮችን ያስተናግዳል። ሰባተኛው ዙር የዳይመንድ ሊግ ውድድር ሰኔ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በፈረንሳይ ርዕሰ መዲና ፓሪስ ይካሄዳል። በአፍሪካ፣ እስያና አውሮፓ ከተሞች የሚካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በቤልጂየም ብራሰልስ ፍጻሜውን ያገኛል። የዳይመንድ ሊግ ውድድር እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ2010 ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን ከ1998 ጀምሮ ሲካሄድ የነበረውን የጎልደን ሊግ ውድድር የተካ ነው።