የኪነ ጥበብ ስራዎች ስለ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ምን ይላሉ? - ኢዜአ አማርኛ
የኪነ ጥበብ ስራዎች ስለ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ምን ይላሉ?
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2011 የኪነ ጥበብ ስራዎች በኢትዮጵያ የጋራ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ዙሪያ ምን ይላሉ? የምድረ ቀደምቷ አገር ህዝቦች ለሺህ ዓመታት ዘመናት የአብሮነት ጉዟቸው እንደ ድርና ማግ የተሳሰረ የጋራ የታሪክ፣ ኃይማኖት፣ ባህል እሴቶች አሻራ አላቸው ሲሉ በርካቶች ይናገራሉ። በኪነ ጥበብ ዘርፎች በሙዚቃ፣ በስነ ስዕልና ፊልም የኪነ ጥበብ መስኮች የጋራ የሆኑ አገራዊ እሴቶችን በማንጸባረቅ ረገድ ምን ሚና ተጫውተዋል የሚለውን ኢዜአ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን አነጋግሯል። የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩ እንደሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ብሔረሰቡ ብዝሃነት ሁሉ ሙዚቃውም የተለያየ ነው። ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ባህላዊ ሙዚቃ ስልቶች ባለቤት መሆኗን ገልጾ፤ ኢትዮጵያኑም ባህላዊ ሙዚቃ ወዳጅ፣ በአገራቸው ሙዚቃ ላይም ትኩረት የሚያደርጉ ናቸው ይላል። 'ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ ነው' የሚለው ባለሙያው በተለይ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ቋንቋው ቢለያይም ተመሳሳይ ቅኝት ስላላቸው በየትም ቦታና ጎራ ሊደመጡ የሚችሉ ናቸው ብሏል። የኢትዮጵያ ሙዚቃና ሙዚቀኞች ለህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ለአገር አንድነት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሙዚቃ ቃና ሊደሰት እንደሚችል ይገልጻል። ሰው በዘርና ቋንቋ ተለያይቶ ፍጅት ውስጥ ቢገባም ሙዚቃ ግን ለየትኛውም ወገን ስሜት ሊሰጥ የሚችል ጥበብ እንደሆነ አብራርቶ፤ እስካሁንም የኢትዮጵያ ሙዚቃ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጉላት ሚናው ትልቅ መሆኑን ይገልጻል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ወጣት ሙዚቀኞች የተለያዩ የብሄረሰቦችን ሙዚቃዎች በመቀየጥ ስራቸውን እያቀረቡ እንደሆነ በመግለጽ፤ በሙዚቃው መስክ ኢትዮጵያዊነትን ይበልጥ እንዲጎላ ያደርጋል ባይ ነው። 'ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የራሷ የአሳሳል ዘዴ ባለቤት ናት' የምትለው የኢትዮጵያ ሴት ሰዓሊያን ማህበር ፕሬዝዳንት ሰዓሊ ሩት አድማሱ በበኩሏ ስነ ስዕል ጥበብ ሃይማኖታዊ፣ማህበራዊ፣ ባህላዊ ድርጊቶችን ለትውልድ የተላለፈበት መሳሪያ መሆኑን ትናገራለች። "ስዕል የትናንት ታሪክን የምታጠናበት፣ ዛሬን የምገልጽበት፣ ወደፊት የምትገምትበትና በስራዎችህ የምታወጣበት ነው" የምትለው ሰዓሊዋ፤ ስዕል የማህበረሰቡ የታሪክ ማስተላለፊያ፣ እሴቱን ለትውልድ ማሻገሪያ ነው ብላለች። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያዊያን ሰዓሊያን የጥንቶችም ሆኑ የዛሬዎች አብሮነትን፣ ታሪክን፣ ባህልን በቀለማት ቅርጾች ቀምረው በአንድ የስዕል ሰሌዳ ላይ ለእይታ እንዲመች አድርገው ሃሳቦችን እንደሚያስቀምጡ ትገልጻለች። ኢትዮጵያዊያን በማንነት፣ በኃይማኖት፣ በባህል እሴቶች የተወራረሱና የተጋመዱ እንደሆኑ የሚገልጸው የፊልም ሰሪዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ደሳለኝ ኃይሉ ነው። ፊልምና ቴአትር አገራዊ እንደ ድርና ማግ የተጣበቀን የጋራ እሴት ማንነት ከማጉላት አንጻር ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጾ፣ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የፊልም ቴአትር ኢንዱስትሪ የጋራ እሴት አገራዊ ማንነትን ከማንጸባረቅ ረገድ ይበልጥ መስራት እንዳለበት ያምናል። የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ አገሪቱ ከቁሳዊ ልማት ጎን ለጎን ለሰብዓዊ ልማት ትኩረት መስጠት አለባት ይላሉ። የኪነ ጥበበ ሰዎችም አገርን፣ ህዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉ፣ አንድነትንና የጋራ እሴት የሚያንጸባርቁ የጥበብና የማስተዋል ስራዎችን መስራት ይጠበቀባቸዋል ባይ ናቸው። አገራዊ ሰላምና አንድነት ለማምጣትም ለኪነ ጥበቡ ዘርፍ በመንግስት በኩል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ነው የሚገልጹት። የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ልዩነትን የማይፈጥር ሙዚቃ፣ ስዕል፣ ፊልምና ሌሎች የጥበብ አይነቶችን መስራት፣ አንድነት፣ ፍቅርና የጋራ ታሪክ ላይ ያተኮሩ ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው መልክት አስተላልፈዋል።