የነቀምቴ ከተማ የንግድ ማህበረሰብ ለሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ከኮማንድ ፖስት ጋር እንሰራለን አሉ - ኢዜአ አማርኛ
የነቀምቴ ከተማ የንግድ ማህበረሰብ ለሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ከኮማንድ ፖስት ጋር እንሰራለን አሉ
ነቀምቴ ሰኔ 15/2011 የነቀምቴ ከተማ የንግድ ማህበረሰብ በከተማው ሰላምን ለማረጋጋትና ለመጠበቅ ከኮማንድ ፖስት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ። ማህበረሰቡ ትናንት በአካባቢው ከተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንዳረጋገጡት የከተማው ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ተቀናጅተው ለመሥራት ተዘጋጅተዋል። ከንግድ ማህበረሰብ አባላት መካከል አቶ ብርሃኑ ሃብቴ በሰጡት አስተያየት የፀጥታ ኃይሎች መለያ አልባሳት አመሳሰለው በመልበስ ሰላም የሚያናጉ፣በዝርፍያና ስርቆት ላይ የተሰማሩ ኃይሎችን ለሕግ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። ዶክተር ዓለምፀሐይ ተስፋ በሰጡት አስተያየት ባለሃብቱ መስራትና ሃብት ማፍራት የሚችለው ሰላም ሲኖር መሆኑን አስረድተው፣የፀጥታ ኃይሉን ሰላምን ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካት ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል። ለውጡን ለማስቀጠል የንግዱ ማህበረሰብ፣ባለሃብቶች፣ቄሮዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣አባገዳዎችና ምሁራን ሰላምና መረጋጋት በማስፈን ድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል። ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ተሳታፊ በበኩላቸው ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን የሚፈልገው ኃይል ሥራ አጥ ወገኖችን ለመጠቀም ጥረት እያደረገ በመሆኑ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ ትኩረት በመስጠት እኩይ ዓላማውን ማክሸፍ ያስፈልጋል ብለዋል። የምስራቅ ወለጋ ዞን ኮማንድ ፖስት ኃላፊ ብርጋዲዬር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደ ኪዳን እንደተናገሩት ለአካባቢው ሰላም መስፈን የአካባቢው ኅብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ሰላምን ለማረጋገጥ በየደረጃው ከሚገኝ አመራርና ከኅብረተሰቡ ጋር በመመካከር እንደሚሰሩም አስታውቀዋል። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ካቢኔ አባል አቶ አህመድ አባግሳ በበኩላቸው የሰላም ጉዳይ የመኖርና አለመኖር ጉዳይ በመሆኑ በከተማውና በአካባቢው የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የጋራ ጥረት እንዲደረግ አሳስበዋል። በዚህም ሰላሙን የሚያናጉትን ወገኖች ለሕግ ማቅረብ ድርሻን መወጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።