ቀጥታ፡

የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በጋራ የመኖር ጽኑ ፍላጎት አለው…ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

ሰኔ15/2011 የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ብሔር ብሄረሰቦች ጋር በመከባበርና በመቻቻል በጋራ ለመኖር ፍላጎት ያለው መሆኑን የክልሉ ምክትል ርእሰ-መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ገለጹ። በየአመቱ ሰኔ 15 ቀን የሚከበረውን የሰማዕታት ቀን በክልል ደረጃ በሃውዜን ከተማ ዛሬ በድምቀት ተከብሯል። በበዓሉ ላይ የተገኙት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ እንዳሉት የዛሬ 31ዓመት በሃውዜን ከተማ በአንድ ጀምበር ከራሱ መንግስት በማይጠበቅ ሁኔታ በርካታ ንጹሐን በግፍ ተጨፍጭፈዋል። ይህም በማንኛውም ወገን ሊፈፀም የማይገባና አስነዋሪ ድርጊት በማስታወስ በየዓመቱ ሰኔ 15 እንደሚከበር ተናግረዋል። የኢትዮጰያ ብሔርና ብሔረሰቦች ለዘመናት ያህል ተቻችለውና ተከባብረው የኖሩ መሆናቸውን የተናገሩት ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ “አሁን ግን ከኢትዮጵያ ፍላጎት ውጭ የሆነ የሰላም እጦት አጋጥሟል” ብለዋል። አሁንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ ሆነው ህገ-መንግስቱ እንዲከበርና የተጀመረው የህዳሴ ጉዞ እንዲቀጥል ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል። “የትግራይ ህዝብ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ንብረቱ ሲዘረፍ ሲቃጠል ሲገደልና ሲታሰር በትዕግስት የተመለከተው ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በጋራ ለመኖር ካለው ጽኑ ፍላጎት ነው”ብለዋል። “የትግራይ ህዝብ ከአማራ ህዝብ በደም የተሳሰረ እንጂ በበደል የሚፈላለጉ ህዝቦች አይደሉም” ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በየጊዜው እያጋጠመ ያለው ያልተገባ ነገር የጥቂት ፖለቲከኞች እንጂ የህዝቡ ፍላጎት እንዳልሆነ ተናግረዋል። “በየዓመቱ ሰኔ 15 የሰማእታት ቀን ስናከብር በሃውዜን የተጨፈጨፉ ንፅሐን ዜጎችና በትጥቅ ትግሉ የተሰው ታጋዮችን ብቻ ሳይሆን አብረው አንድ ጉድጓድ የተቀበሩ የሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ሰማእታትን ጭምር ነው” ብለዋል። እንዲሁም በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ላይ የነበረው ግጭት ወደ ህጋዊ መስመር እንዲያመራ የሀገራቸውን ሉአላዊነት ለማስከበር መስዋእትነት የከፈሉ ጀግኖችም በእለቱ የሚዘከሩ መሆኑን ገልጸዋል። “የሀውዜን ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጎይቶም ፍሰሐ በበኩላቸው በተከፈለው መስዋእትነት በተገኘው ድል የወረዳው ህዝብ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ ሆኗል” ብለዋል። በወረዳው የ65 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ፣አገናኝ መንገዶች መገንባት የሰማእታቱ ውጤት መሆኑንም አስረድተዋል። በበዓሉ ላይ ከ20ሺህ በላይ የወረዳው ህዝብና እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም