የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊጉን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እየመራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊጉን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እየመራ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2011 በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መቐለ ሰብዓ እንደርታን በማሸነፍ የሊጉን መሪነት ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ተረክቧል። ዛሬ በፕሪሚየር ሊጉ የ19ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል። በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መቐለ ሰብዓ እንደርታን 34 ለ 29 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ውጤቱንም ተከትሎ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነጥቡን ወደ 30 ከፍ በማድረግ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ መሪነቱን መረከብ ችሏል። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ተመሳሳይ 30 ነጥብ ቢኖራቸውም ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተሻለ የግብ ክፍያ ስላለው በአንደኝነት ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ችሏል። ተሸናፊው መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ24 ነጥብ በነበረበት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግን ዋንጫ ለማንሳት በሚደረገው ፉክክር በቀጣይ መርሃ ግብር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከጎንደር ከተማ የሚጫወት ሲሆን ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከመቐለ ሰብዓ እንደርታና ከከምባታ ዱራሜ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል። ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ያሉትን ቀሪ ሁለት ጨዋታዎችን ካሸነፈ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሲሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሊጉ አሸናፊ ለመሆን የቀረውን አንድ ጨዋታ ማሸነፍና የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን መሸነፍ ይጠብቃል። ዱራሜ ላይ በተደረገ ሌላ የሊጉ ጨዋታ ከምባታ ዱራሜ ጎንደር ከተማን 28 ለ 20 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በ19ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር ፌደራል ፖሊስ ከድሬዳዋ ከተማ እና ፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከቡታጅራ ከተማ ጨዋታቸውን ማድረግ ነበረባቸው። ድሬዳዋ ከተማ በፋይናንስ ችግር ምክንያት ራሱን ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጭ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን ቡታጅራ ከተማ በተደጋጋሚ በጨዋታ ሜዳዎች ባለመገኘት ፎርፌ እየተሰጠበት በመሆኑ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ ክለቡን ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጭ እንዲሆን ውሳኔ ማስተላለፉም ይታወሳል። በውድድሩ ደንብ መሰረት ፌደራል ፖሊስ እና ፌደራል ማረሚያ ቤቶች የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 የፎርፌ ውጤት አግኝተዋል። ድሬዳዋ ከተማ እና ቡታጅራ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ውጭ መሆናቸውን ተከትሎ በሊጉ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ ስምንት ዝቅ ብሏል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዘንድሮ ሲካሄድ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። በ2009 ዓ.ም ፕሪሚየር ሊጉ ሲጀመር መከላከያ የመጀመሪያ አሸናፊ የነበረ ሲሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የ2010 ዓ.ም አሸናፊ አንደሆነ የሚታወስ ነው።