የ905 ነፃ የጥሪ ማዕከልን በማዘመን በአዲስ መልክ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ሊደረግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የ905 ነፃ የጥሪ ማዕከልን በማዘመን በአዲስ መልክ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ሊደረግ ነው
የኤሌክትሪክ ብልሽትና ማቋረጥን በማስመልከት ለማሳወቅ ነፃ አገልግሎት የሚሰጠው 905 የጥሪ ማዕከልን በአዲስ መተግበሪያ (ሶፍትዌር) በማዘመን በአዲስ መልክ ስራ ሊጀምር ነው። ከኅብረተሰቡ ተደጋጋሚ ቅሬታ የሚቀርብበትን የኤሌክትሪክ ብልሽት ማስመዝገቢያ ነፃ የስልክ ጥሪ መስመር ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሶፍትዌር በማጎልበት ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ መልክ ስራ የሚጀምር መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል። ማዕከሉ በአዲስ መልክ ስራ ሲጀምር የአገልግሎቱን ዓይነትና አቅም በእጥፍ የሚያሳድግ መሆኑም ታውቋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አክሊል ባህታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከዚህ በፊት በኅብረተሰቡ ቅሬታ ሲነሳበት የነበረው 905 የነፃ የስልክ መስመር የሚሰጠውን አገልግሎት በዐይነትና በጥራት ለማሳደግ አገልግሎቱን ከኢትዮ ቴሌኮም ተረክቦ እየሠራ ነው። ማዕከሉ ቀደም ሲል ዋና አገልግሎቱን የሚሰጠው በኢትዮ ቴሌኮም በተከራየነው መስመርና መሠረተ ልማት በመሆኑ በአንድ ጊዜ የሚያስተናግደው የአንድ ጊዜ ጥሪ ከ40 የማይበልጥ ከመሆኑም በተጨማሪ አገልግሎቱን የሚያገኙት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብቻ እንደነበሩ አስረድተዋል። የጥሪ መስመሩ የአገልግሎት ጥራቱም ኋላ ቀርና አነስተኛ በመሆኑ በመስሪያ ቤቱ ላይ በርካታ ቅሬታ ሲፈጥር እንደነበር ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል። አሁን ግን የአገልግሎት አሰጣጡን ከቴሌ ላይ ሙሉ ለሙሉ በመረከብ ደረጃውን የጠበቀ የጥሪ ማስተናገጃ ማዕከል ተገንብቷል ብለዋል። ደንበኞች ላይ ቅሬታ ሲፈጥር የነበረው የጥሪ መሰመር አገልግሎትን የሚያሳልጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ አለ የተባለ አዲስ ሶፍትዌር መገጠሙንም ተናግረዋል። ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ/ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው አዲሱ የ905 ነፃ የጥሪ መስመር በፊት ያስተናግድ የነበረውን የደንበኛ ቁጥር ከ40 ወደ 80 አሳድጓል። አዲሱ የ905 የነፃ የጥሪ መስመር ከኤሌክትሪክ መስመር ብልሽት ማስመዝገብ በተጨማሪ ደንበኛው የቆጠረበትን (የተጠቀመውን) የመብራት ፍጆታ ሂሳብ መጠየቅ የሚያስችሉ ተጨማሪ አገልግሎቶችንም ሊሰጥ እንዲችል ተደርጓል ብለዋል። አዲሱን አገልግሎት በሰው ሃይል ለማሟላትም 320 የሚሆኑ አዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ተማሪዎች ቅጥር ተፈጽሞ ወደ ስልጠና ገብተዋል። አገልግሎቱን ለመስጠት ከተቀጠሩት የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን መካከል 70 ከመቶ የሚሆኑት የኤሌክትሪክ ምህንድስና ተማሪዎች መሆናቸውንም አቶ አክሊል አስረድተዋል። ስልጠናውን ሲከታተሉ ከነበሩት መካከል በኤሌክትሮ መካኒካል ምህንድስና የሰለጠነው ወጣት ሚኒሊክ ብርሃኑና በኤሌክትሪክና ኮምፒተር ምህንድስና የተመረቀችው ወጣት ለግሽ ልዑል አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል። በአስተያየታቸውም እየተሰጣቸው ያለው ስልጠና በአግባቡ እየተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረው፤ ኅብረተሰቡ የሚያነሳውን ቅሬታ በመፍታት ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ከቅሬታ የጸዱና ቀልጣፋ እንዲሆኑ ለማድረግ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ መላኩ ታዬ ናቸው። በቅርቡ የጥራት ደረጃውን አሳድጎ ወደ ሥራ እንደሚገባው የ905 የብልሽት ማስመዝገቢያ የስልክ መስመር ያሉ ተጨማሪ አገልግሎቶችን ለደንበኞች ለማቅርብ በርካታ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውንም ጠቅሰዋል።