በኦሮሚያ ክልል ከ300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች የሚተከሉባቸው ጉድጓዶች ነገ ይዘጋጃሉ

99
ሰኔ15/2011 በኦሮሚያ ክልል ነገ በሁሉም አካባቢዎች ከ 300 ሚሊዮን በላይ ችግኞች የሚተከሉበት የጉድጓድ ቁፋሮ ፕሮግራም ይካሄዳል፡፡ የጉድጓድ ቁፋሮ ፕሮግራሙ ነገ ከ 12 ሰአት ጀምሮ ከክልል እስከ ቀበሌ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ ነዉ የሚካሄደዉ፡፡ የጉድጓድ ቁፋሮ ፕሮግራሙ ኣላማ በአንድ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያስተላለፉትን የዘንድሮዉን የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ጥሪን ለማሳካት ሲሆን በሌላ በኩል ባለፈዉ አመት ሰኔ 16 በተካሄደዉ ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ዶክተር አብይ ላይ የተቃጣን የግድያ ሙከራ ለማክሸፍ የተሰዉና የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉን ወገኖች ለማሰብ ነዉ፡፡ የችግኝ ጉድጓድ ቁፋሮዉ ከ2 ሚሊዮን ሄክታር ስፋት በላይ በሚሸፍን መሬት ላይ የሚከናወን ይሆናል፡፡ በፕሮግራሙ እያንዳንዱ ተሳታፊ በነፍስ ወከፍ 40 ጉድጓድ እንዲያዘጋጅ ይደረጋል፡፡ ዘንድሮ በኦሮሚያ ክልል የአየር ንብረት ለዉጥን ሊታደጉ የሚችሉ፣ ለእንስሳት መኖና የፍራፍሬ ዝርያ ያላቸዉ 2 ቢሊዮን የሚጠጋ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም