የአለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር የ300 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የአለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር የ300 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አካሄደ
ሰኔ 14/2011የገንዘብ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ በዋን ወሽ ፕሮጀክት ለሚከናወኑ የንጹሁ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ለግልና ለአካበቢ ንጽህና መጠበቂያ የሚውል የ300 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ከአለም ባንክ ጋር አካሄደ። የተገኘው ገንዘብ ሶስት ሚሊዮን ህዝብ የንጽሁ ውሃ አቅርቦት እንዲያገኝ እንዲሁም ከዚህ በፊት ፕሮጀክቱ ያልሰራባቸው አዳዲስ አካባቢዎች የሚኖሩ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ህዝብ የንጽህና መጠበቂያ ተቋማትና አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል። ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴና በኢትዮጵያ የአለም ባንክ ዳይሬክተር ሚስ ካርሎይን ተርክ በዛሬው እለት ተፈራርመዋል። ብድሩ በረጅም ጊዜ የሚከፈል ሲሆን የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እንደሚውል አቶ አህመድ በስምምነቱ ወቅት ገልጸዋል። ''በተለይም የንጹሁ ውሃ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ፣የግልና የአካባቢን ንጽህና አገልግሎት ለማጎልበትና ለማሳደግ እንዲሁም የውሃ ሃብት አጠቃቀምና አስተዳደርን የሚያጠናክሩ ስራዎች ይሰሩበታል'' ብለዋል። የገጠር፣ የከተማ፣ አገልግሎት የሚሰጡ በተለይም የትምህርትና የጤና ተቋማት የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ የግልና የአካባቢ ንጽህና ለመጠበቅ፣ በአየር ንብረት ለውጥ በተደጋጋሚ ለውሃ እጥረት የሚጋለጡ አካባቢዎችን የውሃ አጠቃቀም ለማስተካከልና አቅምን ለመገንባት እንደሚውል ሚኒስትሩ አክለዋል። የአለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስ ካርሎይን ተርክ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የዋን ወሽ ፕሮጀክት በአገሪቷ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን 52 ሚሊዮን ህዝብ የንጹህ ውሃ አቅርቦት ተጠቃሚ እንዲሆን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ ወስጥ 10 ሚሊዮን ህዝብ በአለም ባንክ የፋይናንስ ድጋፍ የተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል። ''የአሁኑ የብድር ስምምነት አዳዲስ አካባቢዎችን ተደራሽ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል'' ሲሉ ተናግረዋል። በመሆኑም ስምምነቱ በንጹሁ ውሃ አቅርቦት ሁለት ሚሊዮን የገጠርና አንድ ሚሊዮን በአጠቃላይ ሶስት ሚሊዮን ህዝብ ተደራሽ የሚያደርግ ሲሆን 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የገጠርና 400 ሺህ የከተማ የህብረተሰብ ክፍል የንጽህና መጠበቂያ ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል። ይህም 80 በመቶ የሚሆኑ ቀበሌዎች መፀዳጃ እንዲያገኙና 2 ሺህ 800 የጤናና የትምህርት ተቋማት ደግሞ የተሻለ የዋን ወሽ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸው አብራርተዋል።