ቀጥታ፡

በኦሮሚያ የአዳዲስ አሰራሮችና የቴክኖሎጂዎችን ተደራሽነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው

አዳማ ሰኔ 14/201 1የክልሉን ግብርና ለማዘመንና በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በመካናይዜሽንና ቴክኖሎጂ አገልግሎት ማስፋፋት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኦሮሚያ ገጠር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ። የክልሉ የግብርና ምርምር ማዕከላት የሚያፈልቁት አዳዲስ አሰራሮችና የቴክኖሎጂ ግኝቶች ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ማድረስ በሚቻልበት ሂደት ላይ ያተኮረ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ እየተካሔደ ነው ። በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኦሮሚያ ገጠር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደገለጹት የክልሉን ግብርና ለማዘመንና በዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በመካናይዜሽንና ቴክኖሎጂ አገልግሎት ማስፋት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ። "በተለይም የምርት ግብዓት አቅርቦት፣ የቴክኖሎጂና አዳዲስ አሰራሮች፣ የሰው ኃይል ልማትና የመፈፀም ብቃት ማሳደግ ልዩ ትኩረት ያገኙ ጉዳዮች ናቸው" ብለዋል ። የክልሉን የግብርና ሽግግር ለማሳካት ለቀጣዩ 15 ዓመታት የሚቆይ ፎኖተ ካርታና የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ በዘርፉ ሙሁራን በማስተቸትና በግብዓት በማዳበር በአሁኑ ወቅት ወደ ትግበራ መገባቱን አስረድተዋል ። የሴክተሩን ተቋማዊ አደረጃጀት መለወጥ፣ የኤክስቴሽን አገልግሎት ክለሳ፣ የዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት የቴክኖሎጂ ማፍለቅ አቅም ማሳደግ በትኩረት ከሚሰራባቸው ዘርፎች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው ተብሏል ። በተጨማሪም የገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ከመሰረቱ ማሻሻል፣ ለገበያና ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ምርቶች በጥራትና በብዛት ማምረት፣ የመስኖ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃም ከቀዳሚ አጀንዳዎች የሚካተቱ ናቸው ። የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋቶ እሲሞ በበኩላቸው የምርምር ማዕከሉ የክልሉን የግብርና ዘርፍ ለማሻገር የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በዘንድሮ ዓመት ብቻ ከ20 በላይ አዳዲስ የሰብል ምርጥ ዘሮችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚው ህብረተሰብ እያደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል። "አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ከድህነት ለማለቀቅ የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮችን ጨምሮ ከ400 በላይ የቴክኖሎጂ ግኝቶችን በምርምር በማውጣት ለተጠቃሚው ለማድረስ በሂደት ላይ ይገኛል" ብለዋል። በተለይም የግሉ ዘርፍ በቴክኖሎጂ ማላመድና ማስፋፋት ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ከመንግስት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አቶ ፋቶ ተናግረዋል። "በመካናይዜሽን፣ በቴክኖሎጂና በምርጥ ዘር ብዜት የግሉን ሴክተር በስፋት ማሳተፍ ካልተቻለ የዘርፉ ሽግግር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጠራል" ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የማሽላና አቀንጨራ ተመራማሪ ዶክተር ታዬ ተሰማ ናቸው። የቴክኖሎጂና ምርጥ ዘር ማሻሻያ ሥርዓት መዘርጋት አለበት ያሉት ዶክተር ታዬ ከምርት ማሳደጊያ ጀምሮ በጥራትና በብዜት ላይ የተቀናጀ አሰራር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት በዓመት በአማካይ ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እንደሚያስፈልግ የገለፁት ተመራማሪው በተጨባጭ እየቀረበ ያለው ከ1 ሚሊዮን ኩንታል ያልበለጠ መሆኑን ጠቁመዋል ። ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ከአካባቢ ስነ ምህዳር ጋር የሚስማሙ የቅድመ መስራች ዘሮች ብዜት ላይ በስፋት መስራት እንዳለባቸው አስገዝበዋል። በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ ከፌዴራልና ከክልል የግብርና ሴክተር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች የተወጣጡ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆኖዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም