ቀጥታ፡

ሁለተኛው የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ውጤት አላመጣም ተባለ

ሰኔ 14/2011ሁለተኛው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ። በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ የኃይል ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስቆም ያለመ 8ኛው የባለድርሻ አካላት ፎረም በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ኮሚሽነር ወይዘሮ መሰረት ማሞ በፎረሙ ላይ እንደገለጹት ሁለተኛው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም ። "ለመረሃግብሩ አለመሳካት በሀገረራቱ እየተበከተ የመጣው የዜጎች መፈናቀል ነው" ያሉት ኮሚሽነሯ በግጭትና መፈናቀሉ ሴቶችና ህፃናት ይበልጥ ለሰብዓዊ መብት ጥሰት መጋለጣቸውን ተናግረዋል። በግጭት ወቅት በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰው ማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን ያመለከቱት ወይዘሮ መሰረት "ይህን ችግር ለማስቆም  ለሰላምና ለዜጎች ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተን መስራት አለብን" ብለዋል። ፎረሙ የሁለተኛው ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር አፈፃፀምና የተገኘው ውጤት በመገምገም የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል። በኮሚሽኑ የሴቶችና ህፃናት ዳይሬክተር ወይዘሮ ትህውን ሽፈራው በበኩላቸው "በሀገሪቷ አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥና የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ በቅንጅት መስራት አለብን ብለዋል። "ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ መፈናቀል ከዓለም በቀዳሚዎቹ ተርታ ትሰለፋለች" ያሉት ዳይሬክተሯ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተፈናቀሉት 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ 1ሚሊዮን የሚሆኑት ህፃናት መሆናቸውን ጠቁመዋል ። አጠቃላይ ከተፈናቀሉት ዜጎች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና ህፃናት መሆናቸውን ጠቅሰው መፈናቀሉ በተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብትና የስነ ልቦና ጫና እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል። "መንግስት መፈናቀልን ለማስቆም እየወሰደ ባለው እርምጃ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ተጋላጭነትና ጥቃት እንዲቀንስ ያግዛል" ብለዋል። በእስካሁኑ ሂደት ከ1 ሚሊዮን 800 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ቄያቸው እንዲመለስ መደረጉ የመንግስት ቁርጠኝነት የታከለበት መሆኑን ጠቅሰው ወደ አካባቢያቸው የተመለሱ ዜጎች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዳይጋለጡ ጠንክራ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። የተቀሩትንም በፍጥነት ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ያለውን ጥረት ኮሚሽኑ እንደሚያደንቅ ጠቅሰው በዘላቂነት ለማቋቋም ከወዲሁ ርብርብ መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ገነት አባተ በበኩላቸው ምክር ቤቱ ከህግ ክፍተት፣ ከአፈፃፀምና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች እንዲፈቱ  ለኮሚሽኑ የሥራ ስኬት አስፈለጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ኮሚሽኑ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ትግራይ፣ ሶማሌና ቤንሻንጉል ጉሙዝ  ክልሎች በተፈናቃዮች ጊዜያዊ ማቆያዎች ተገኝቶ ያደረገው ጥናት መንግስት ተፈናቃዮችን በፍጥነት ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ውጤታማ ሥራ መከናወኑን መመልከት ችሏል ። በቀጣይነት ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን በሙሉ አቅማቸው አንደሚሰሩ የሥራ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል ። በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ላይ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ የፍትሀ አካላትና የፎረሙ አባላት ተሳታፊ ሆኖዋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም