በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 12 ሚሊዮን ወጣቶች ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 12 ሚሊዮን ወጣቶች ይሳተፋሉ
ሰኔ 14/2011በመላ ሃገሪቱ 12 ሚሊዮን ወጣቶችን በዘንድሮ ክረምት በጎፈቃድ አገልግሎት ለማሳተፍ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱን የሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወይዘሮ ያለም ጸጋይ ገለጹ። የ2011ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የመክፈቻ ፕሮግራም በአዳማ ከተማ በችግኝ ተከላና በደም ልገሳ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ በአዳማ ከተማ በሚገኘው ሚግራ ተራራ ላይ በመገኘት ችግኝ በመትከል ፕሮግራሙን ያስጀመሩት ሚኒስትሯ እንዳስታወቁት እስከ መጪው ጳጉሜ ድረስ የሚያከናውኑት የበጎ ፈቀድ አገልግሎት 4 ቢሊዮን ብር የሚገመት አስተዋፅኦ ይኖረዋል ። ወጣቶች በሚያከናውኗቸው ልዩ ልዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችም 22 ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ “የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በሃገሪቱ ባህል እየሆነ መጥቷል”ያሉት ወይዘሮ ያለም ወጣቶቹ አገልግሎቱን ሲሰጡ የህብረተሰቡን መልካም እሴቶች በመቅስም ምሳሌ ከመሆንና ልማታዊ ተሳትፏቸውን ከማበረታት ባለፈ ችግሮችን የመቋቋም ልምድ እንዲያዳብሩ እንደሚረዳም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባር በበኩሉ በክረምት ወራት ወጣቶች ሊሰሯቸው የሚፈልጓቸውን ተግባራት በመለየት ቀደም ብሎ ምዝገባ መካሄዱን ገልጿል። “የሀገሪቱ ወጣቶች በያገባኛል ስሜት በሁሉም መስክ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ነው” ያለው ወጣት ታረቀኝ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱና ዋነኛው መሆኑን ጠቁሟል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላለፈውን በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ በአግባቡ በመትከልና በመንከባከብም በየደረጃው ርብርብ እንደሚደረግ አስታውቋል። በችግኝ ተከላው ከተሳተፉት መካከል በአዳማ ከተማ ሚግራ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አማን ጃምቦ እንደተናገረው በስራው በመሳተፉ የመንፈስ እርካታን ማግኘት ችሏል። በመሰል እንቅስቃሴዎች ላይ ከጓደኞቹ ጋር የሚያደርገውን ተሳትፎም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል። ዛሬ በአዳማ ከተማ በተካሔደው የችግኝ ተከላና ደም ልገሳ ፕሮግራም ላይ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የወጣት አደረጃጀቶች ተሳትፈዋል።