ቀጥታ፡

የወንዞች ፍሰት አስተማማኝና ዘላቂ  እንዲሆን የደን ሽፋን ወሳኝ ነው

ሰኔ 14/2011 የወንዞች ፍሰት አስተማማኝና ዘላቂ እንዲሆን የደን ሽፋን ወሳኝ መሆኑን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ፡፡ የድርቅ ተጋላጭነትን ለመከላከል  የደንና ቋሚ ሰብሎችን ማልማት  ልዩ ትኩረት የሚሻ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በኮሚሽኑ የደን ልማት ዘርፍ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክትር ተፈራ መንግስቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የወንዞች ተፋሰስና የአየር ንብረት ጤናማ መሆን ለቀጠናው ሀገራትም አስተዋጾኦ ስለሚያበረክት ከጎረቤት  ሃገራት ጋር መልካም ግንኙነት እንዲጎለብት ያስችላል ብለዋል፡፡ የችግኝ ተከላ ልማት ግብርናውንና የሃይል አቅርቦት ማጎልበትን ጨምሮ ለሌሎች ሁለንተናዊ ብልጽግና ጉልህ ሚና እንዳለውም ተገልጿል። በተለይ የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ከውሃ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የችግኝ ልማት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት፡፡ የደን ልማት ከዝናብ ስርጭት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ስላለው ለግብርና ምርት እድገትና ለሃይል አቅርቦት መጎልበት ሚናው የጎላ  መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምንጭ መሬትና ውሃ በመሆኑ ከሌሎች ሃገሮች በተለየ የደን ልማት እንደሚያስፈልጋትና የመሬት አቀማመጧም ለዚሁ አመቺ መሆኑን ዶክትር ተፈራ ይናገራሉ፡፡ የደን ልማት የዝናብ ስርጭትን ለማስተካከል አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች በደን በመሸፈን የአየር ንብርት ለውጥን መከላከል እንደሚያስችልም አብራርተዋል፡፡ ’’ከ20 አመታት በፊት በቂ ችግኝ ተተክሎ ቢሆን ኖሮ የድርቅ ስጋትና ተያያዥ ችግሮች መቅረፍ ይቻል  ነበር’’ ያሉት አስተባባሪው፤ በሚቀጥሉት 20 ና 30 አመታት ትኩረት ሰጥቶ መስራት  አስፈላጊ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ የደን ልማትን ከሌሎች የልማት ግቦች ጋር በማስተሳሰር የአስር አመት የደን ልማት ፕሮግራም ተነድፎ እየተሰራ መሆኑንም ነው ዶክተር ተፈራ የገለጹት፡፡ በፕሮግራሙ በከተማና በገጠር የደን ልማት መካተቱን ጠቁመው ለአረንጓዴ ልማትና   ኢኮኖሚያ እድገት ፋይዳ እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡ በኮሚሽኑ የብሄራዊ ሬድ ፕላስ  ሴክሬታሪያት  አስተባባሪ ዶክተር ይበቱ ሞገስ፤ በቀደምት ዘመናት የተተከሉ ችግኞች እንክብካቤ ተደርጎለት ቢሆን፤ በተለያየ ገዜ የሚከሰተውን ድርቅ  መከላከል  ይቻል እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በሀገሪቱ ዘላቂ ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው የደን ልማት  ሲኖር ብቻ መሆኑን ያብራሩት ዶክተር ይበቱ፤ ግድቦች በደለል የሚሞሉት በአየር ንብረት ለውጥ በመሆኑ የሀይል ማመንጫዎች ህልውናን  ለማረጋገጥ  የደን ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተያዘው የክረምት ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት በሀገር አቀፍ ደረጃ  4 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም