ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የቼስ ቡድን በምስራቅ አፍሪካ የዞን 4 ነጥብ 2 የቼስ ውድድር ለመሳተፍ ወደ ጂቡቲ አቀና

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ማለዳ ወደ ጂቡቲ አቀና። አዲስ አበባ ሰኔ 2/2010 በምስራቅ አፍሪካ የዞን 4 ነጥብ 2 የቼስ ውድድር የሚሳተፈው የአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሽን በየዓመቱ የሚያካሂደው ይህ ውድድር ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሰኔ 12 ቀን 2010 ዓም ድረስ የሚካሄድ ሲሆን ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ በአራት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ትወከላለች። በወንዶች ለይኩን መስፍን፣ አይዳኙም ግዛቸው፣ ኤርሚያስ ተክለማርያም እና እንዳለ መኮንን፤ በሴቶች ልደት አባተ እና ፌቨን ገብረመስቀል በውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ። የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ በላይነህ ለኢዜአ እንደገለጹት ስድስቱ ተወዳዳሪዎች የተመረጡት በአገር አቀፉ የቼስ የግል የበላይነት ውድድር ባስመዘገቡት ውጤት ነው። የጂቡቲው ውድድር ተሳታፊዎች ከመጋቢት 19 እስከ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በተካሄደው የቼስ የግል የበላይነት ውድድር በየተወዳደሩበት ዘርፍ የተሻለ ውጤት ማስመዝገባቸውን አስታውሰዋል። የምስራቅ አፍሪካ የዞን 4 ነጥብ 2 የቼስ ውድድር የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ዛሬ ሲከናወን፤ ከነገ ጀምሮ ጨዋታዎች መካሄድ ይጀምራሉ። በውድድሩ በወንዶች ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡ ተወዳዳሪዎች የአንድ ሺህ፣ የ800 እና 600 ዶላር ሽልማት ሲያገኙ ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡት ሴቶች ደግሞ 750፣ 500 እና 250 ዶላር እንደሚበረከት ገልጸዋል። በአጠቃላይ በውድድሩ የ4 ሺህ 300 ዶላር ሽልማት መዘጋጀቱንና በሁለቱም ጾታዎች የሚያሸንፉ ተወዳዳሪዎች በ2018 የዓለም የቼስ የአገራት ሻምፒዮና ላይ አፍሪካን ወክለው የመሳተፍ ዕድል ያገኛሉ ብለዋል። በውድድሩ ላይ በምስራቅ አፍሪካ ዞን 4 ነጥብ 2 ውድድር አዘጋጇ ጂቡቲ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ ታንዛንያ፣ ሱዳን፣ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ሲሸልስና ግብጽ ይሳተፋሉ። የምስራቅ አፍሪካ የዞን 4 ነጥብ 2 የቼስ ውድድር ባለፈው ዓመት በጅማ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል። ኢትዮጵያ እና የቼስ ስፖርት የረጅም ዓመት ቁርኝት እንዳላቸው ይነገራል። ቼስ ስፖርት ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት «ሰንጠረዥ» በሚል ስያሜ በኢትዮጵያ ውስጥ ይዘወተር እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም