የህንድና የኢትዮጵያን የንግድ ልውውጥ ሚዛን ለመጠበቅ እየተሰራ ነው - በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
የህንድና የኢትዮጵያን የንግድ ልውውጥ ሚዛን ለመጠበቅ እየተሰራ ነው - በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር
አዲስ አበባ ሰኔ13/2013 የህንድና የኢትዮጵያ የንግድ ልውውጥ ሚዛኑን ጠብቆ ለማስኬድ አዳዲስ የንግድ ግንኙነት አመራጮች እየተፈለጉ መሆኑን በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ገለጹ። አምባሳደር አኑራግ ስሪቫስታቫ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሳተፉትን የህንድ ኩባንያዎች ቁጥራቸውን ለመጨመርም በዘርፉ ያለውን ማነቆ ለማፍታት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየሰራን ነው ብለዋል። አምባሳደሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና ህንድ ከጥንታዊ የሥልጣኔ ዘመናቸው ጀምሮ እስከሁኑ ዘመናዊ ዓለም ድረስ የዘለቀ የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አላቸው። በተለይም ንግድን በተመለከተ ኢትዮጵያ በአክሱም ሥልጣኔ በአዱሊስ ወደብን ከህንድ ነጋዴዎች ጋር ቅመማ ቅመምና የዝሆን ጥርስን በረጅም ርቀት የንግድ እንቅስቃሴ ተሳስረው ነበር። ይህ አይነቱ የንግድ ልውውጥ ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንስቶ ደግሞ ይበልጥ በመጠናከሩ በአሁኑ ወቅት የአገራቱ የንግድ ልውውጥ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በአመዛኙ ወደ ህንድ የግብርና ውጤቶች ስትልክ በአንጻሩ ደግሞ መድሃኒቶች፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ማሽኖችና ተሽከርካሪዎችን ደግሞ ከህንድ እንደምታስመጣ መረጃዎች ያሳያሉ። የህንድ ፕሬዝዳንት ራም ናት ኮቪንዳ ከሁለት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የተቋቋመው የጋራ የንግድ ኮሚሽንም የንግድ ልውውጡ እንዲጠናከር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ያም ሆኖ ኢትዮጵያ ወደ ህንድ ከምትልከው ይልቅ የምታስገባው በመብለጡ የንግድ ልውውጡ ሚዛኑን ባለመጠበቁ ይህንን ለማቅናት አዳዲስ የንግድ አማራጮችን እየተጠኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለይም የጋራ ኮሚቴው ጉዳዩ አሳሳቢ መዋቅራዊ መሆኑን በመረዳት ለመፍትሄው እየተረባረበ መሆኑን ገልጸዋል። በሌላ በኩል የህንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎ ከ100 ዓመት በፊትም በኢትዮጵያ በሥራ መሰማራታቸውን ነው የተናገሩት። ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ ሥራቸውን እንደቀጠሉና በተለይም ባለፉት 10 አመታት ጊዜ ውስጥ ብዛት ያላቸው የህንድ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ጠቁመዋል። አብዛኞቹም በጨርቃ ጨርቅና ዘርፍ ላይ በስፋት መግባታቸውን በመግለጽ። በአሁኑ ወቅት ከ600 በላይ የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ተሰማርተዋል። 60 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በማምረቻ ዘርፍ የተሰማሩ ናቸው። ይህም ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚጠጋ መዋዕለ ነዋይ ያፈሳሉ ተብሎ ይገመታል። ከ52 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የሥራ እድል ተፈጥሯል። ይህንንም ተከትሎ ህንድን በኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ከተሰማሩ ሦስት የውጭ አገራት አንዷ እንድትሆን ማስቻሉን ነው አምባሳደሩ የገለጹት። ይሁን እንጂ ይህም ማደግ እንዳለበት በማመን በቀጣይ ይብልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል። በአንጻሩ ህንድ በርካታ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ባለቤት መሆኗን ገልጸው ይህንን የካበት ልምድ ለኢትዮጵያ ለማቅረብ ባላት ፍላጎት መሰረት ለጋዜጠኞች የሥልጠና መርሃ-ግብር እየሰጠች መሆኑም ጠቁመዋል። ይህም ሁለቱ አገራት ከሁለት ከሁለት ዓመታት በፊት በሳይንስና ቴክኖሎጂ የደረሱትን ሥምምነት ተከትሎ መሆኑን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም የዚህ የሥልጠና መርሃ-ግብር ተጠቃሚ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መሆኑንም ነው አምባሳደሩ ያስታወሱት። በተጨማሪም ኢትዮጵያና ህንድ ጠንካራ የሚባል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመው በተለይም በየቀኑ ወደ ህንድ በረራ መኖሩን ይህንን እንደሚያመላክት ነው ያስረዱት። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በመሆኗ፤ ህንድም ልክ እንደ ሌሎቹ አገራት ኢትዮጵያን 'የአፍሪካ መግቢያ በር' አድርጋ እንደምትጠቀምባት ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እስከ ስድስት ሺ የሚጠጉ የህንድ ማኅበረሰብ አንደሚገኝ ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያሳያል። በምስራቅ አፍሪካም ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥና ዘላቂ የልማት እንቅስቃሴዎች አንዲሳለጡ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመሆን ህንድ እየሰራች መሆኑን ጠቁመዋል።