ቀጥታ፡

ኡጋንዳ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ፍላጎት አላቸው

ኡጋንዳ ሰኔ 2/2010 ኡጋንዳ ውስጥ ለረጅም ዓመታት የኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ወደ አገራቸው ተመልሰው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሳተፍ  ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ። ኡጋንዳ ካምፓላ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ትናንት ምሽት  ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ካምፓላ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር በሁለትዮሽ፣ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። መሪዎቹ ሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚ ትስስርን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር  በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይም ተስማምተዋል። በኡጋንዳ ውስጥ ስለሚኖሩና ስለሚሰሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላትም ሀሳብ ተለዋውጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይም ማምሻውን ኡጋንዳ ውስጥ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋር አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ተወያይተዋል። የማህበረሰቡ አባላት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤ ይህም በመሆኑ ወደ አገራቸው ተመልሰው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሳተፍ ፍላጎት አላቸው። በኡጋንዳ ለ27 ዓመታት የኖሩት ባለሀብት አቶ ዮሐንስ በርሄ እንደሚሉት፤ የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት ይከታተላሉ፤ አሁን በአገሪቷ ያለው ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱንና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተገንዝበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ በውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን ጥሪ በመቀበል ወደ አገራቸው መመለስ ይፈልጋሉ። “በአገሪቷ ውስጥ ባለሀብቱን የማያሰሩ ህጎች መቀየርና ውስብስብ ቢሮክራሲያዊ አሰራሮች መፈታት አለባቸው” በማለት ነው ሀሳባቸውን የገለጹት። ለረጅም ዓመታት ኡጋንዳ የኖሩት ወይዘሮ ሰብለ ገብሩ በበኩላቸው፤ "በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ለውጥ ውስጥ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መሳተፍ ይኖርባቸዋል" ብለዋል። በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች እንዳያጋጥሟቸው ከወዲሁ ጠንክሮ መሰራት አስፈላጊ መሆኑን ነው ያመለከቱት። “ውስብስቡ ቢሮክራሲ ከተፈታና ሁኔታዎች ከተመቻቹ በአገራችን ለውጥ እናመጣለን” ብለዋል። ኡጋንዳ ለዘጠኝ ዓመታት የቆዩትና በግል ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ብርሃኑ ገመቹ እንደሚሉት፤ "አሁን በአገር ውስጥ የሚታየው ለውጥ ተስፋ ሰጪ ነው፤ ይህም ወደ ህብረተሰቡ ወርዶ ሕግና ስርዓትን መሰረት ባደረገ መልኩ በተግባር ሊተረጎም ይገባል"።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም