የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተጠሪ ተቋማት እየተባበሩኝ አይደለም አለ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተጠሪ ተቋማት እየተባበሩኝ አይደለም አለ
ሰኔ 13/2011 የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም 41 የመንግስት ተጠሪ ተቋማት ለመተባበር ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል። ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ 41 የመንግስት ተጠሪ ተቋማት ለትብብር ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ባቀረቡት የ11 ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ገልጸዋል። በህዝብ እንባ ጠባቂ አዋጅ ቁጥር 211/1992 አንቀጽ 38 በመተባበር ግዴታ መሰረት ማንኛውም ሰው አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ይደነግጋል። ይሁንና በፌዴራልና በክልል የሚገኙ 41 የመንግስት ተጠሪ ተቋማት በቀረቡ አቤቱታዎች ላይ የተሰጣቸውን የመፍትሄ ሀሳብ ለመፈጸም ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ዶክተር እንዳለ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። ለአብነት የገቢዎች ሚኒስቴር በቀድሞ የፊናንስ ፖሊስ አባላት በእነ አቶ በቀለ ተስፋዬ የተቀመጠን ገንዘብ ለመመለስ ፍቃደኛ አለመሆኑን ጠቅሰዋል። የአማራ ክልል የዋግ ህምራ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደርም በተከዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክት ግንባታ መሬታቸው በውሃ ለተዋጠ 24 ሰዎች የካሳ ክፍያ ምላሽ አልሰጠም። የሀዋሳ ማዘጋጃ ቤት ለ25 ሰዎች የምትክ ቦታና የካሳ ክፍያ አለመፈጸሙ፣በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሀረርጌ ዞንና የሜታ ወረዳ አስተዳደሮች ለጨለንቆ ሰማዕታት ሃውልት መስሪያ 62 ሰዎች ያለምንም የካሳ ክፍያ ከመኖሪያ ቤታቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል። ተቋሙ የሰጠውን የመፍትሄ ሀሳብ ተግባራዊ ያላደረጉ አስፈጻሚ አካላትን ለምክር ቤቱ የህግ፣ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በልዩ ሪፖርት ማቅረቡንም ዋና እንባ ጠባቂው አብራርተዋል። እንደ ዶክተር እንዳለ ገለጻ የፍላጎት ማነስና የተጠያቂነት አሰራር ስርዓት አለመኖር ተጠሪ ተቋማቱ ከተቋማቸው ጋር እንዳይተባበሩ አድርጓል። በሌላ በኩል ተቋሙ ባለፉት 11 ወራት አንድ ሺህ 653 የአቤቱታ መዝገቦችን መርምሯል። ከእነዚህ መዝገቦች 871 የአስተዳደር በደል አለመኖሩ ተረጋግጦ ውሳኔ ሲያገኙ 181 አስተዳደራዊ በደል መኖሩ ተረጋግጦ በማስማማት መፍትሄ ተሰጥቷቸዋል። በ70 መዝገቦች የአስተዳደር በደል መፈጸሙ ተረጋግጦ የመፍትሄ ሀሳብ፣በ77 ደግሞ አስተዳደራዊ በደል መፈጸሙ ተረጋግጦ በቅድመ ምርመራ አፋጣኝ ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል። እንዲሁም 48 መዝገቦች በአቤቱታ አቅራቢዎችና በተለያዩ ምክንያቶች የተቋረጡ መሆናቸውን ዋና እንባ ጠባቂው አብራርተዋል። አቤቱታዎቹ የይዞታ፣ የስራ፣ ተገቢ አገልግሎት ያለማግኘት፣ የቤት ጥያቄ፣ ከትምህርት ከጡረታና ከካሳ ክፍያ እንዲሁም ከመረጃ ክልከላ ጋር በተያያዘ የቀረቡ ናቸው።