ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች እየሰለጠኑ ነው

አዲስ አበባ ሰኔ13/2011 ከኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የተውጣጡ ደጋፊዎች በስራ ፈጠራና ውጤታማነት ዙሪያ በአዲስ አበባ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው። ስልጠናው የሚያተኩረው ወጣቶች የአመለካከት ለውጥ በመፍጠር እራሳቸውን ለስራ ዝግጁ የሚያደርጉበትና አዳዲስ የስራ መስክ መፍጠር የሚያስችል ነው ተብሏል። የስልጠና አሰጣጡም በአነቃቂ ንግግሮቻቸውና አዝናኝ አቀራረባቸው ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። በዘርፉ የካበተ ልምድ ካላቸው መካከል አቶ ዩሃንስ ጣሰው ስልጠናውን ከሚሰጡት ባለሙያዎች መካከል ናቸው። እንደ አቶ ዩሃንስ ገለፃ መሰል ስልጠናዎች ወጣቶች በአገር ግንባታ ሂደት የጎላ ሚና እንዲኖራቸው ያደርጋል። ይሁን እንጂ ከስልጠና በኋላ መንግስት ወጣቶቹ ያለ ቢሮክራሲ ወደ ስራ የሚገቡበትን ምቹ ሁኔታ ካልፈጠረ የታሰበው ውጤት ላይመጣ ይችላል ብለዋል። ከሰልጣኞቹ መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች እንዳሉት ስልጠናው በማዝናናት ትምህርት የሚገኝበት በመሆኑ ለለውጥ እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል። ከስልጠናው በኋላም ለስኬትና ውጤታማነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፍቃደኞች ማስተባበሪያ ቢሮ የወጣቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማስተባበሪያ ክፍል ቡድን መሪ አቶ ሙላቱ አበበ ስልጠናው ለወጣቶቹ ላቅ ያለ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። በስልጠናው ላይ የተሳተፉት በሁለቱ ክለብ በደጋፊ አስተባባሪዎች በኩል ለስልጠናው ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል። ስልጠናው እየተሰጠ ያለው ከጥቃቅንና አንስተኛ ኢንተርፕራይዝ ቢሮና አዲስ ብድርና ቁጠባ እንዲሁም ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ነው። ስልጠናው በሶስት ዙር የሚሰጥ ሲሆን በመጀመሪያ ዙር ለሶስት ቀናት ስልጠና ሲሰጣቸው የነበሩ ከ100 በላይ ወጣቶች ዛሬ የሚያጠናቅቁ ይሆናል። የሁለተኛ ዙር ስልጠና ነገ የሚጀመር ሲሆን የመጨረሻው ዙር ስልጠናም የሚቀጥል ሲሆን በሁሉም ዙሮች በአጠቃለይ 350 ወጣቶች የሚሰለጥኑ ይሆናል። ከስልጠናው በኋላ በሚፈልጉት የሙያ መስክና ከተማ አስተዳደሩ ቢሰማሩበት የተሻለ ነው ባለው የሙያ መስክ እንደሚሰማሩም ታውቋል። በአራት ኪሎ የስፖርት ትምህርትና ስልጠና ማዕከል እየተሰጠ ባለው ስልጠና ከሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች በተጨማሪ የብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎችም ይገኛሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም