ተፈታኞቹ ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂውን ትግበራ ላይ የድርሻቸውን አየተወጡ ነው

50
ነገሌ/ፍቼ/ጭሮ ሰኔ 12 / 2011 በኦሮሚያ ክልል ሦስት ዞኖች የዘንድሮ ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች ችግኞችን በመትከል የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂውን ትግበራ ድርሻቸውን አየተወጡ መሆናቸውን ገለጹ። ከተማሪዎቹ አንዳንዶቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት  ችግኞቹን የተከሉት ድርቅን የሚቋቋምና የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተያዘውን ጥረት ለማሳካት ነው። በቦረና ዞን የኤሎየ ወረዳ 200 ያህል የ10ኛ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ከ5 ሺህ የሚበልጡ ችግኞች መትከላቸውን የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቦነያ ሀለኬ ተናግረዋል። የ12ኛ ክፍል ተፈታኟ ዓይናለም ኤርሚያስ 40 ችግኞች መትከሏንና ውጤት ሰምሮላት  ዩኒቨርሲቲ ከገባች በየዓመቱ ለዕረፍት ስትመጣ ችግኞችን ለመትከልና ለመንከባከብ ቃል ገብታለች፡፡ የፍቼ ከተማ ተፈታኞች በትምህርት ቤታቸው ቅጥር ግቢ ችግኞችን ተክለዋል ። ከወጣቶቹ መካከል የፍቼ ቀለምና መሰናዶ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ወጣት ህሊና ደረጀ በረሃማነትን ለመቀነስና የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ የተጀመረው ትግል ከግብ እንዲደርስ ተሳትፎዋን ታጠናክራለች ። በተለይ በአካባቢዋና በትምህርት ቤቷ አቅሟ እስከሚፈቅደው ድረስ በክረምት ወራት ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ኃላፊነቷን ለመወጣት እንደተዘጋጀችም ገልጻለች። የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ ሚኪያስ ግሩም በበኩሉ አካባቢውን ውብና ማራኪ ለማድረግ ችግኞችን ከመትከል በተጨማሪ የፅዳት ስራዎችን ለማከናወን በከተማው አስተዳደሩ የሚወጣውን ፕሮግራም እየተጠባበቀ መሆኑን ተናግሯል፡፡ የፍቼ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ በላይ ወልደ ጻዲቅ  በክረምት ወቅት ከ10 ሺህ በላይ ችግኞች በተማሪዎችና በመምህራን በተመረጡ ቦታዎች እንደሚተከሉ ተናግረዋል ። በምዕራብ ሐረርጌ ዞን  በጭሮ ከተማ ጨርጨር መሰናዶ  የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ፈተናቸውንም ሲያጠናቅቁ  ችግኞችን ተክለዋል። ከተማሪዎቹ  ሰላማዊት ታምራት የ አየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከልና በረሃማነትን ለመከላከል ያለው ድርሻ በመገንዘብ በተከላው መሳተፏን ገልጻለች። ይህ በእንዲህ እንዳለ የጭሮ ኤፍ ኤም ም 101ነጥብ 1 ሬዲዮ ጣቢያ ሥራ መጀመርን ምክንያት በማድረግ የኦሮሚያ ክልልና የምዕራብ ሐረርጌ ዞን  አመራሮች በቂልሶ ተራራ ችግኞችን ተክለዋል። የኦሮሚያ ገቢዎች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጫልቱ ሳሊ እንደገለጹት ተከላው ''40 ችግኝ ለአንድ ሰው'' የሚለውን መርሐ ግብር በመከተልና የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ከግብ ለማድረስ ነው ብለዋል።                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም