ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው የመመለሱ ተግባር እንዲጠናከር አሳሰበ

ዲላ ሰኔ 12/2011 ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው ለመመለስ የተጀመረው ጥረት አበረታች ቢሆንም፤ወደ መኖሪያቸው ላልተመለሱ ዜጎች ትኩረት እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አሳሰበ፡፡ ተመላሾች ከስጋት ነጻ ሆነው እንዲኖሩ ሁሉም አካላት ድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቋል፡፡ በኮሚሽኑ የሴቶችና ህጻናት ኮሚሽነር መሰረት ማሞ የሚመራ ቡድን በጌዴኦ ዞን ወደ ቄያቸው ያልተመለሱ ተፈናቃዮች በጎበኘበት ወቅት እንዳሉት ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመው መኖሪያቸው ለመመለስ የሚደረገው እንቅስቃሴ መጠናከር አለበት። በአገሪቱ የሚታየው መፈናቀል ካደረሰው ችግር ስፋት አኳያ ትኩረት እንደሚያሻው  ያመለከቱት ኮሚሽነሯ፣በተለይም ህጻናትን ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ትኩረት እንዲሰጥ አስገንዝበዋል። በአገሪቱ አሁን ያለው መፈናቀል የሰብዓዊነት ቀውስ ነው ያሉት ኮሚሽነር መሠረት ፣ መንግሥት የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቄያቸው ለመመለስና በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት ኮሚሽኑ ያደንቃል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከ70 ዓመታት በፊት የዜጎቿን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ ዓለም አቀፍ ስምምነት መፈረሟን አስታውሰው፣ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸው ተነፍጎ ለአካላዊና ሞራላዊ ጉዳት የሚጋለጡበት ሁኔታ መቀየር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ ኮሚሽኑ ተፈናቃዮችን ወደ ቄያቸው የመመለሱ ሂደትን በመፈተሽና ከሰብዓዊ መብት አንጻር ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ወደ ቄያቸው የተመለሱ ዜጎች ከስጋት ነጻ ሆነው እንዲኖሩ በተለይ በወረዳና ቀበሌ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት አመራሮች ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ተወካይ ወይዘሮ ምስጋና ዋቀዮ በበኩላቸው መንግሥትና ሕዝብ ባደረጉት ጥረት ዜጎች ወደ ቄያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት 16 ወራት ከምስራቅ ጉጂ ዞን ተፈናቅለው በዲላ ከተማ የሚገኙትን ተፈናቃዮች የሁለቱ ዞኖች አመራሮች ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል። በከተማዋ የሚገኙት ተፈናቃዮች ለተለያዩ አካላዊና ሞራላዊ ቀውስ እንደተጋለጡም አስረድተዋል፡፡ በመጠለያ ከሚገኙ ህጻናት መካከል ሰርካለም ብርሃኑ እንደገለጸችው ከአንድ አመት በላይ ከምትኖርበት ምስራቅ ጉጂ ዞን ተፈናቅላ በዲላ ከተማ ቆይታለች፡፡ በዚህም የአራተኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሕይወቷን እየመራች መሆኗን ገልጻለች፡፡ መንግሥት ወደ ቄያቸው መልሷቸው  በሰላም ለመኖርና ትምህርቷን ለመቀጠል እንደምትፈልግም ተናግራለች፡፡ በዲላ መጠለያ ጣቢያ ከምስራቅ ጉጂ ዞን የተፈናቀሉ ስምንት ሺህ የሚደርሱ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ታውቋል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም