ቀጥታ፡

የጉጂ ዞን አርሶ አደሮች መጤ ተምችን ለመከላከል መድኃኒት እንዲቀርብላቸው ጠየቁ

ሰኔ 12/2011 በጉጂ ዞን በበቆሎ ሰብል ላይ የተከሰተውን መጤ ተምች በእጅ በመልቀም ብቻ ለመከላከል አስቸጋሪ እየሆነ በመምጣቱ በቂ መድኃኒት ይቅረብልን ሲሉ አርሶ አደሮች ጠየቁ ። በጉጂ ዞን ግርጃ ወረዳ የቀጢና ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዳዊት ሶካ እንደገለጹት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ የዘሩት የበቆሎ ቡቃያ በመጤ ተምቹ መጠቃቱን ገልጸዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውን አስተባብረው በእጅ በመልቀም ለመከላከል ያደረጉት ጥረት በቂ ባለመሆኑ "ቡቃያው የከፋ ጉዳት ይደርስበታል የሚል ስጋት አድሮብኛል" ብለዋል፡፡ ከመንግስት የፀረ ተባይ መድኃኒት እንዲቀርብላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም ይመጣል ከሚል የዘለለ መፍትሔ እንዳላገኙ ተናግረዋል ። መጤ ተምቹን በባህላዊና በዘመናዊ መንገድ መከላከል ካልተቻለ የሚያደርሰው ጉዳትም ሆነ የመዛመት እድሉ አሳሳቢ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት እንዳደረባቸውም ገልፀዋል ። ሌላው የኤዲሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኡቱራ ኤዴማ በበኩላቸው በአካባቢው የዝናቡ መጠን ጋብ በማለቱ ተምቹ በተለይ የበቆሎ ሰብሉን በፍጥነት እያጠቃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ተምቹ በፍጥነት እየተራባና እየተስፋፋ በመሆኑ በመድኃኒት ርጭት ካልታገዘ በስተቀር በእጅ በመልቀም ብቻ ለማጥፋት አስቸጋሪ በመሆኑ ለጸረ ተባይ መድኃኒት ለአቅርቦት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል ። በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት የበቆሎ ሰብል አብዛኛው በተምቹ በመጠቃቱ በእጅ በመልቀም ለመከላከል ያደረጉት ጥረት ውጤታማ መሆን እንዳልቻለም ተናግረዋል። የጉጂ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት በበኩሉ እንደገለፀው መጤ ተምቹ በዞኑ በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች በ1 ሺህ 91 ሄክታር መሬት በለማ የበቆሎ ሰብል ላይ ተከስቷል፡፡ በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ቦነያ ሁቃ ለኢዜአ እንደተናገሩት የተምቹን ስርጭትና የሚያደርሰውን ጉዳት በመድኃኒትና በሰው ጉልበት ለመከላከል ርብርብ እየተደረገ ነው ፡፡ የበልግ ዝናብ መቀነሱን ተከትሎ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ የተከሰተው ተምች በከፍተኛ ሁኔታ የበቆሎ ሰብልን እያጠቃ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አቶ ቦኖያ እንዳሉት በአርሶ አደሩና በግብርና ባለሙያዎች ትብብር እስካሁን ድረስ በ510 ሄክታር ማሳ ላይ የለማ የበቆሎ ሰብልን ከተምቹ መከላከል ተችሏል፡፡ ተምቹን ለመከላከል 800 ባለሙያዎችና በእጅ የሚለቅሙ ከ2 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ገልጸው አስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ የዋለው መድኃኒት 27 ሊትር ብቻ መሆኑን አስረድተዋል ። "የተምች ወረርሽኙን ሙሉ በሙሉ ለመከላከል 5 ሺህ ሊትር ጸረ ተባይ መድኃኒት እንዲቀርብ ለክልሉ መንግስት ጥያቄ ቀርቦ መልስ እየተጠበቀ ነው" ብለዋል ። በዞኑ በበልግ አዝመራ 160 ሺህ 433 ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን ከእዚህም ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም