የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መስፋፋት ያልተነገረ ታሪክና ባህል ለማስተዋወቅ ያስችላል- የሐረርና የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መስፋፋት ያልተነገረ ታሪክና ባህል ለማስተዋወቅ ያስችላል- የሐረርና የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ነዋሪዎች
ሐረር ሰኔ 12/2011 የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መስፋፋት ያልተነገረ ታሪክና ባህል ለማስተዋወቅ እንደሚያስችል በሐረር ከተማና የምስራቅ ሐረርጌ ዞን የኅብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ። የኦሮሚያ ብሮካስቲንግ ኔትወርክ(ኦ ቢ ኤን) በሐረር ያቋቋመው ቅርንጫፍ ተመርቋል። በምረቃው ሥነ ሥርዓት የታደሙ የኅብረተሰቡ ክፍሎች እንደተናገሩት የመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት መጠናከርና መስፋፋት መረጃን የሕዝቦችን ያልተነገረ ታሪክና ባህል ለመዳሰስ ያስችላል፡ በተጨማሪም መረጃ በአካባቢው ቋንቋዎች በማድረስም አስተዋጽኦው የላቀ መሆኑን አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ሬዲዮ የቀድሞ የሐረር ቅርንጫፍ የኦሮምኛ ቋንቋ ጋዜጠኛ ወይዘሮ አልፊያ ሃጂ በከተማዋ ሬዲዮ ጣቢያው መከፈቱ መረጃ የአካባቢውን ቋንቋና ባህልን መሠረት ባደረገ መልኩ ለሕዝቡ ለማድረስና ድምፁንም ለማሰማት ያስችለዋል ይላሉ፡፡ የምስራቁ የአገሪቱ ክፍል ሕዝብ ለሬዲዮ አገልግሎት አዲስ አንዳልሆነና ይልቁንም አገልግሎቱን በማጣቱ ቅሬታ እንደነበረው የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዋ ፣ሬዲዮ ጣቢያው መከፈቱ የሕዝቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያጎለብታል ብለዋል፡፡ '' በስርጭት ወቅትም በአካባቢውን ባህል፣እሴትና ሃብት አውጥቶ ማሳየት ይገባል።ኅብረተሰቡንም የሚመስሉ አስተማሪና አዝናኝ የሆኑ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀትና ማቅረብ ተገቢ ነው።እኛ የቀደሞ ባለሙያዎችም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን'' ብለዋል፡፡ ከባቢሌ ከተማ የመጡት አቶ ተፈራ ሳሙኤል ሬዲዮ ጣቢያው በሰላም ፣ በአንድነት እንዲሁም በማህበራዊ አገልግሎት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ወይዘሮ ሚስራ አብዱራህማን የተባሉ አስተያየት ሰጪ'' ከሬዲዮ ጣቢያው ብዙ እንጠብቃለን በአካባቢው ብዙ የተደበቁ ጉዳዮች አሉ በተለይም ከባህልና ታሪክ አንፃር በርካታ ያልተዳሰሱና ሊነገሩ የሚገቡ ጉዳዮች ስላሉ ሊሰራበት ይገባል'' ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም ሴቶችንና ህፃናትን የተመለከቱ ጉዳዮች በአካባቢው ቋንቋዎች መስተናገድ እንደሚገባቸው ገልጸዋል። የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊና የኦ ቢ ኤን የቦርድ አባል ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ጣቢያው ለኅብረተሰቡ የመረጃ ምንጭ ከመሆን ባሻገር፤በልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች የሚያደርገውን ተሳትፎ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል። ሕዝብና መንግሥትን በማቀራረብ ሚናውን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል። ሬዲዮ ጣቢያው የሕዝቡን ፍላጎት መረዳት ወገኝተኝነቱን የሚያረጋግጡ ተግባራትን እንደሚያጠናክር የተናገሩት ደግሞ የኦ ቢ ኤን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ አስራት ናቸው። በምረቃው ወቅት የኦሮሚያና ሐረሪ ክልሎች ከፍተኛ የአመራር አካላት፣የቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮ የሐረር ቅርንጫፍ የኦሮምኛ ክፍል ጋዜጠኞች፣አርቲስቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።