ቀጥታ፡

ጭሮ ኤፍኤም 101 ነጥብ አንድ ሬዲዮ ጣቢያ ስራ ጀመረ

ሰኔ 11/2011 የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ/ኦቢኤን/ የህዝብ ድምጽ በመሆን የመረጃ ተደራሽነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ጭሮ ኤፍኤም101 ነጥብ አንድ ሬድዮ ጣቢያ ስርጭት ዛሬ ተመርቆ ስራ ጀምሯል። በምረቃው ላይ የተገኙት የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊና የኦቢኤን የቦርድ አባል ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንደተናገሩት የሬዴዮ ጣቢያው የአካባቢው ህብረተሰብ ሃብት በመሆን እድገቱን ለማፋጠን የድርሻውን የሚሰራ ነው። በዚህም ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ፈጥኖ ለህብረተሰቡ በማድረስ የህዝብ ድምጽነቱን በተጠናከረ መልክ በመስራት እንደሚያረጋግጥ ጠቁመዋል። የኦቢኤን የበላይ ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ አስራት በበኩላቸው ጭሮ ኤፍኤም101 ነጥብ አንድ በማህበረሰብ ጥያቄ መሰረት የተገነባ በመሆኑ የአካባቢያዊውን ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት ያደረጉ ስራዎችን በማከናወን እንደሚያገለግል ገልጸዋል። የጭሮ ኤፍ ኤም101 ነጥብ አንድ ስራ አሰኪያጅ ጋዜጠኛ መሀመድ ኡስማን በበኩሉ ጣቢያው ከዞኑ 17 ወረዳዎች በተጨማሪ በሀረር፣ በአዲስ አበባ፣ በሶማሊያና ከፊል ባሌ እንዲሁም ከፊል አፋር ክልልን በስርጭቱ አድማሱ በመሸፈን በቀን ለስድስት ሰዓታት አየር ላይ እንደሚውል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም