ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አቅምን ለማሳደግ የሚያስችል የ40 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ

ሰኔ 11/2011 የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን ምርጫ የማስፈጸም አቅምን ለማጠናከር የሚያስችል የ40 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ስምምነት ዛሬ በመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ተፈረመ። ቦርዱን ለማጠናከር ለተቀረፀው ፕሮጀክት ከሚያስፈልገው 40 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ሁለት ሚሊዮን ዶላሩን የልማት ፕሮግራሙ መድቧል። እንደዚሁም 34 ነጥብ 6 ሚሊዬን ዶላሩ በተለያዩ የልማት አጋሮች ቃል የተገባ ሲሆን ቀሪው 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በፕሮጀክቱ የትግበራ ወቅት የሚሰበሰብ መሆኑም ተገልጿል። ስምምነቱን የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ቱራሃን ሳሌህ  እና የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱኳን ሚደቅሳ ናቸው። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በአገሪቱ የተካሄደው ለውጥ ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ለማስቻል ተቋማትን ማጠናከር ዋነኛው ነው። በተለይም በምርጫ ቦርድ ውስጥ ጠንካራ የምርጫ ማስተግበሪያ ስርዓት መዘርጋትና በምርጫ ሂደት ውስጥም አዳዲስና ዘመናዊ የምርጫ አስተዳደርን ማስተዋወቅ የሚያስችል አቅም እንዲኖር ማድረግ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ገልፀዋል። የ40 ሚሊዬን ዶላር ፕሮጀክቱ የምርጫ ሂደት ግልፅነትን፣ውጤታማነትንና አሳታፊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ እንደሆነም አብራርተዋል። በተጨማሪም በምርጫ ሂደት መገናኛ ብዙኃንና ሌሎቸ ባለድርሻ አካላት ለማሳተፍና ተቋማዊ አቅምን በማጎልበት በምርጫ ወቅት የሚከሰቱ ማናቸውም ግጭቶችን ለመለየት፣ ለመቆጣጠርና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያግዛል። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው እንዳሉት ድጋፉ በምርጫ ቦርዱ እየተከናወነ ያለውን ለውጥ የሚያግዝ ነው። የቦርዱ አዲስ የስራ አመራር ወደስራ ከመጣበት ግዜ ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠንካራ አጋዥ መሆኑን በተግባር እያሳየ ነው ሲሉም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ቱራሃን ሳሌህ ኢትዮጵያ እያከናወነች ካለው የለውጥ ሂደት አኳያ መጪው ምርጫ ስኬታማ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ይህም እውን እንዲሆን ድርጅታቸው የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ተወካዩ ሌሎች ድጋፍ ሰጪ ተቋማትም ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል ብለዋል። ይህም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያ ጎን ለመሆን ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የሚያመላክት ነው ሲሉ ይናገራሉ። ለሶስት ዓመታት የሚካሄደውን ፕሮጀክቱን የሚተገብረው ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም