ቀጥታ፡

የኮሌራ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው ክልሎች 18 የህክምና መስጫ ማዕከላት ተቋቋመ

ሰኔ 11/2011 የኮሌራ ወረርሽኝ በተከሰተባቸው ክልሎች በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለይቶ ለማከም የሚያስችሉ 18 የህክምና ማዕከላት መቋቋማቸውን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ። በአጠቃላይ በአገሪቱ በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 614 መድረሱም ተጠቁሟል። እንደ ኢንስቲትዩቱ ገለጻ፤ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎችን ለማከም በኦሮሚያ ክልል ዘጠኝ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለት፣ በትግራይ ክልል አንድ እንዲሁም በአማራ ክልል ስድስት የህክም መስጫ ማዕከላት ተቋቁሟል። የተቋቋሙት ማዕከላት ይበልጥ ለበሽታው ተጋላጭ ተብለው ለተለዩ 17 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማከምና ክትባት ለመስጠት የሚውሉ ናቸው። ኢንስቲትዩቱ የፌደራል ማረሚያ ቤቶችን፣ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን ማገገሚያዎችን፣ የጎዳና ህጻናት ማገገሚያዎችና አዳሪ ትምህርት ቤቶችን እንዲሁም በወረርሽኙ ህክምና አገልጎሎት ሰጭ ባለሙያዎችን ይበልጥ ለበሽታው በተጋላጭነት ለይቷል። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ እንዳሉት፤ የወረርሽኙን መስፋፋት ለመቆጣጠርና የመድሀኒትና ተያያዥ የህክምና እጥረቶችን ለመቅረፍ ሲባል ክትባቱን ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በቅድሚያ እንዲያገኙ ተደርጓል። ስርጭቱን ለመግታትም  ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከሀይማኖት ተቋማትና በአገሪቱ ከሚገኙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በቅርበት በሁለት ዙር ህክምና ለመስጠት የባለሙያዎች ስልጠና ዝግጅት እየተደረገ ነው። በሁሉም ክልሎች የበሽታውን መንስኤ በጥናት በመለየት የመድሀኒትና ህክምና ግብዓቶች ወደ ህክምና ጣቢያዎች ተልከዋል፤ በአዲስ አበባ ከነገ ጀምሮ የክትባት አገልግሎት እንደሚሰጥና በሁሉም ክልሎች ደግሞ በቀጣይ ሳምንት ይጀምራል ተብሏል። በበሽታው ምክንያትም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ለ16 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት። ወረርሽኙ በዚህ ወቅት በኦሮሚያ ክልል 294 ሰዎችን፣ በአማራ ክልል 198 ሰዎችን፣ በትግራይ 18 ሰዎች እና በአዲስ አበባ ደግሞ በ70 ሰዎች ላይ መታየቱን ገልፀው በአዲስ አበባና ትግራይ ክልል በተዘጋጁ ለይቶ ማቆያዎች የተኛ ታካሚ የለም ተብሏል። የበሽታውን ስርጭት አስመልክተው በአማራ ክልል አሁን ያለው የወረርሽኝ ቁጥር በነበረበት መሆኑን የ13 ቀናት መረጃ ማሳየቱን ገልጸው ''በድሬዳዋም ከኦሮሚያ ክልል ከሄደ አንድ ሰው የበሽታው ምልክት ታይቷል'' ብለዋል። ከኮሌራ በሽታ በተጨማሪ የችኩንጉኒያ ወረርሽኝ በሶማሌ ክልል ተከስቶ 115 ሰዎች ላይ ታይቷል። የወባ ወረርሽኝም በወረርሽኝ መልክ በአገሪቱ የተለያዩ አካባዎች በተለይም በደቡብ ክልል በወላይታ ዞን ስድስት ወረዳዎች በአማራ ክልል ባህርዳር ዙሪያና ደራ ወረዳዎች ተከስቷል። ህብረተሰቡ ለወባ ትንኝ መራባት አመቺ የሆኑ የታቆሩ ውሃዎችን እንዲያፋስስና የአልጋ አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀም አሳስበዋል። የኩፍኝ ወረርሽኝ በአፋር ክልል አሳይታ ወረዳ ተከስቶ 256 ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸውን ዶክተር በየነ ገልጸዋል። በተያያዘም በዲሞክራቲክ ኮንጎና በዩጋንዳ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝን በተመለከተ ኢንስቲትዩቱ ጥብቅ ክትትል እያደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል። የኢቦላ ወረርሽኝ ወደአገሪቱ እንዳይገባ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ እንደሆነ አመልክተዋል። በዚህም በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የተጓዦች የሙቀት መጠን ልየታ እየተካሄደ ሲሆን በጣቢያው በበሽታው የተያዙ መንገደኞች ካጋጠሙ ለይቶ ማከም የሚያስችል ስፍራ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ወደአገሪቱ የሚገቡ ሰዎችም ለ21 ቀናት የህክምና ክትትል እንደሚደረግላቸውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም