ቀጥታ፡

በመንደር ብንሰባሰብም የመሰረት ልማት ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም ---የሰሃላ ወረዳ ነዋሪዎች

ሰኔ 11/2011 በመንደር ብንሰባሰብም የመሰረተ ልማት ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም ሲሉ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰሃላ ወረዳ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል አቶ ይግለጥ ሙላው እንደተናገሩት ቀደም ሲል ይኖሩበት ከነበረው ሰሃላ ወረዳ ጓሮች ጎጥ በመንደር ማሰባሰብ መርሀ ግብር ወደ ፈፋ አካባቢ ሄደው ኑሯቸውን በመምራት ላይ ናቸው። የቀድሞ መኖሪያ አካባቢያቸው ተራራን መሰረት አድርጎ የተመሰረተ ከመሆኑ በተጨማሪ ንጹህየመጠጥ ውሃ፣ የመንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ያልተማሉበት እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡ “መንግስት ባለንበት አካባቢ የጤናም ሆነ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ መሆን እንደማንችል ነግሮን ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በፈፋ አካባቢ በመንደር እንድንሰባሰብ አድርጎናል” ብለዋል፡፡ በዚህም በአካባቢያቸው የጤና ጣቢያ፣ የትምህርት፣ የግብርና ግብአትና የእንስሳት ጤና አገልግሎቶችን ያለምንም እንግልት በቅርበት ማግኘት እንደቻሉ ነው የተናገሩት፡፡ በፈፋ አካባቢ መንገድን መሰረት አድርገው እንደሰፈሩ የገለጹት አቶ ይግለጥ በሰፈሩበት አካባቢ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የስልክ፣ የኢንተርኔትና የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ተናግረዋል። “በአካባቢያችን ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ምክንያት የወንዝ ውሃን ለመጠጥነት ለመጠቀም ተገደናል” ሲሉም ገልጸዋል። የስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ባለመሆናቸውም በተለይ በአደጋ ጊዜ የአምቡላንስ አገልግሎትም ሆነ የተለያዩ እርዳታዎችን ለመጠየቅም ሆነ ለማግኘት እንዳልቻሉ ነው የተናገሩት። በፈፋ ቀበሌ በመንደር ከተሰባሰቡ ወዲህ የተሻለ ኑሮ እየመሩ መሆናቸውን ነው የገለጹት ደግሞ አቶ አባተ ኃይለማሪያም የተባሉ ነዋሪ ናቸው ፡፡ “በመንደር ስንሰባሰብ የስልክ፣ የመብራት እና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ትሆናላችሁ” ተብለን ነበር፤ አስካሁን ግን ተግባራዊ ባለመደረጉ ተቸግረናል” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ ምክንያት የእህል ወፍጮ ፍለጋ በእግር እስከ 5 ሰዓት እንደሚጓዙ ጠቁመው፣ በዚህም ለዕንግልትና ለደራሽ ጎርፍ አደጋ እየተጋለጡ መሆናቸውን ተናግረዋል። መንግስት ይህንን ችግራቸውን ተረድቶ ፈጣን መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ነው አቶ አባተ የጠየቁት። የሰሃላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚሰው ፈንታየ በበኩለቸው የፈፋና አካባቢዋ ነዋሪዎች የስልክ፣ የኢንተርኔትና የመብራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለክልሉ መንግስት ጥያቄ ቢቀርብም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በፈፋ አካባቢ ባለፈው ዓመት ግንባታው የተጠናቀቀው ጤና ጣቢያ የሰው ኃይልና የመድኃኒት አቅርቦት ተሟልቶለት ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ገልጸዋል። “በአካባቢው የስልክ አገልግሎት ባለመኖሩ ህብረተሰቡ ድንገተኛ ሕመምና አደጋ ሲገጥመው ፈጥኖ በመድረስ ተገቢውን ድጋፍ መስጠት አልተቻልም” ብለዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመነጋገር ገመድ አልባ ስልኮች ከጤና ተቋማት ጋር እንዲተሳሰሩ ለማድረግ እንደሚሰራም አመልክተዋል። የንጹህ መጠጥ ውሃን ችግር ለመፍታትም ከዚህ ቀደም የተሰራውና በመስመር ዲዛይን ችግር አገልግሎት መስጠት ያቆመውን በማስተካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደሥራ እንዲገባ የጥገና ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። የብሔረሰብ አስተዳደሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንደወሰን ጌታቸው በበኩላቸው “የፈፋ እና ሌሎች አካባቢዎች የስልክ እና መብራት ተጠቃሚ ለማድረግ አስፈላጊውን ጥናት ተደርጓል” ብለዋል። በቀጣይ ዓመት የፈፋ ቀበሌን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎችን የስልክ እና የመብራት አቅርቦት ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል። በፈፋ እና አካባቢዋ ከ10 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ያሉ ሲሆን በቅርቡም ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለማስገንባት የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው የሚታወስ ነው፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም