ቅዱስ ጊዮርጊስ በአርባ ምንጭ ከተማ 3 ለ0 ተሸነፈ

88
አዲስ አበባ / አርባ ምንጭ ሚያዝያ 22/2010 በ22ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አርባ ምንጭ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን 3 ለ0 አሸንፏል። ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው አርባ ምንጭ ከተማ ዛሬ ማሸነፉን ተከትሎ ደረጃውን ወደ 12ኛ ከፍ ለማድረግም ችሏል። ዛሬ በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ድል የተቀናጀው አርባ ምንጭ ከተማ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እዮብ ማለን ባለፈው ሳምንት ማሰናበቱ የሚታወስ ነው ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ቢቀሩትም የዛሬውን ጨዋታ ቢያሸንፍ ወደ መሪነት የሚጠጋበት እድል ነበረው። ይህን ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለበት አራተኛ ደረጃ ሲቀመጥ ጅማ አባጅፋር፣ መቀሌ ከተማና ደደቢት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ዘንድሮ በውጤት ቀውስ ውስጥ የነበረው አርባ ምንጭ ከነማ ሁለተኛውን አሠልጣኝ ባሰናበተበት ማግስት ጊዮርጊስን መግጠሙ ስጋት የፈጠረ ቢሆንም ጫዋታው በተጀመረ በ3ኛው ደቂቃ የአዞዎቹ አንበል አማኑኤል ጎቤና የመጀመሪያውን ጎል አስቆጥሯል፡፡ ጎሉ በፈጠረው መነቃቃት አዞዎቹ ጫና ፈጥረው በመጫዎች በ38 ኛው ደቂቃ በፀጋዬ አበራ ሁለተኛው ጎል አስቆጥረዋል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ማጠናቀቂያ በሆነው በ45ኛው ደቂቃ አርባ ምንጭ ከነማ ያገኘውን ፍጹም ቅጣት እንዳለ ከበደ ወደ ጎል በመቀየር በ3 ለባዶ ወደ እረፍት አምርተዋል ፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ በሁለቱም ክለቦች ጥሩ የኳስ እንቅስቃሴ ቢታይም ጎል ሳይቆጠር በአርባምንጭ ከነማ 3 ለባዶ አሸናፊነት ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ በሜዳውም ሆነ ከሜዳ ውጭ ጊዮርጊስን ማሸነፍ ከባድ የነበረው የአዞዎቹ ክለብ ከጫዋታ ብልጫ ጋር ማሸነፉ ጣፋጭ ድል መሆኑን የተናገረው ጊዜያዊ የቡድኑ መሪ እና ግብ ጠባቂው ጃክሰን ፊጣ ነው ፡፡ ከወልዋሎ አድግራት 3 ለባዶ ሽንፈት በኋላ ድል መገኘቱን ተከትሎ ለክለቡ ደጋፊዎች ደስታውን የገለጸው ጊዜያዊ የቡድን መሪው በቀጣይም ክለቡን ከወራጅ ቀጠና አውጥቶ በአስተማማኝ ደረጃ ላይ ለማድረስ ጠንካራ የቤት ሥራ እንደሚጠብቃቸው ጠቁሟል ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝ ቫዝ ፒንቶ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረዋል ፡፡ ''በሁለተኛው አጋማሽ ስህተቱን አርመን ተጭነን የተሻለ የኳስ እንቅስቃሴ ብናደርግም ጎል ማስቆጠር አልተቻለም'' ብለዋል፡፡ በቀጣይ በሚኖረው ጨዋታ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በቂ ዝግጅት እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል ፡፡ በተያያዘ ዜና በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ፋሲል ከነማ አዳማ ከተማን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል። ዛሬ ጎንደር ላይ አዳማና ፋሲል ከነማ በመደበኛው ሰዓት ያለምንም ግብ ጨዋታቸውን በማጠናቀቃቸው ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በተሰጠው የመለያ ምት ፋሲል ከነማ አዳማን 6 ለ5 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል። ፋሲል ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ከሶስት ቀን በፊት አዳማ ከተማን አስተናግዶ ጨዋታው ጎል ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም