ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ የኢዜአ ቦርድ አባላትን ሹመት በሙሉ ድምጽ አጸደቀ

አዲስ አበባ ሰኔ 11/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ የቦርድ አባላትን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ። ምክር ቤቱ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅንም መርምሮ አጽድቋል። ዛሬ በተካሄደው 5ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 45ኛ መደበኛ ስብሰባ በቀረበው አጀንዳ መሰረት የቦርድ አባላቱ ተገኝተው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሆኖ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በአዲስ አዋጅ እንደገና መቋቋሙ ይታወሳል። በማቋቋሚያ አዋጁ መሰረትም የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት አማካኝነት ዕጩ የቦርድ አባላትን ዝርዝር ዛሬ ለምክር ቤት አቅርበዋል። ምክር ቤቱም በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስር ዴኤታ በአቶ ታዜር ገብረእግዚአብሄር ሰብሰባቢነት ሰባት የቦርድ አባላትን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። ወይዘሮ ህይወት ሃይሉ ከወጣቶችና ሴቶች ሚኒስቴር ፣ አቶ አብነት ዘርፉና ዶክተር ታምራት ሃይሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፣ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፣ አቶ መስዑድ አደም ከሃይማኖት ጉዳዮች በአባልነት እንዲሁም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሙለታ ያለድምጽ በአባልነት ተሹመዋል። አባላቱም በምክር ቤቱ ፊት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። በተያያዘ ዜና ምክር ቤቱ በንግድ ምዝገባና ፈቃድ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 54/2011 በተመለከተ በንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ አድምጧል። አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ አገልግሎት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ተደራሽ፣ ቀላል፣ ቀልጣፋ፣ ወጭ ቆጣቢና ዘመናዊ የአሰራር ስርዓትን መዘርጋት ለማስቻል መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው አስረድቷል። ምክር ቤቱም በአብላጫ ድመጽ በሶስት ድምጸ ተዐቅቦ መርምሮ አጽድቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም