አሜሪካ ተጨማሪ 1 ሺህ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ልትልክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካ ተጨማሪ 1 ሺህ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ልትልክ ነው
ሰኔ 11/2011 አሜሪካ ተጨማሪ 1 ሺህ ወታደሮችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆኗን አስታወቀች፡፡ የአሜሪካ ተጠባባቂ የመከላከያ ሚኒስትር ፓትሪክ ሻናሃን እንዳሉት ወታደራዊ ስምሪቱ የኢራን ኃይሎች እያሳዩት ላሉት ትንኮሳ ምላሽ ለመስጠት ነው። የዋሽንግተንና የቴህራን ፍጥጫ እንደቀጠለ ነው። የአሜሪካ የባህር ኃይል ባወጣው አዲስ ምስል በኦማን ባህረ ሰላጤ በነዳጅ መርከብ ላይ የተፈፀመው ጥቃት ከኢራን ጋር እንደሚገናኝ ጠቁሟል። ኢራን ትናንት በሰጠችው መግለጫ ከ2015ቱ የኒዩክሌር መርሃ ግብርን የማቆም ስምምነት በከፊል በመውጣት የዩራኒየም ምርቷን እንደምትጨምር ገልጻለች። በመጪው የፈረንጆቹ ሰኔ 27 በስምምነቱ የተጣለውን የምርት መጠን ገደብ እንደምትጥስ ገልጻለች። የአሜሪካ ተጠባባቂ የመከላከያ ሚኒስትር ከኢራን ጋር ጦርነት የመግጠም ፍላጎት እንደሌላቸው ቢገልጹም በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ወታደሮቻቸውን ደህንነት ለመጠበቅ በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ወር በመካከለኛው ምስራቅ ለሚገኙ ወታደሮች ተጨማሪ ኃይል እንዲሰማራ ማዘዛቸው ይታወሳል። ምንጭ፦ቢቢሲ