ቀጥታ፡

የሰቆጣ ከተማ ምክር ቤት በጸጥታ አካላት ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዘ

ሰኔ 10/2011የሰቆጣ ከተማ ምክር ቤት በትላንትናው ዕለት በከተማው የጸጥታ ኃይሎች ላይ የተፈጸመውን የግድያ ወንጀል እንደሚያወግዝ አስታወቀ። ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ባካሄደው አራተኛ አስቸኳይ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በትላንትናው እለት በሶስት የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ላይ የተፈጸመው የግድያ ወንጀል የከተማውን ህዝብ የሚወክል አይደለም። የምክር ቤቱ ዋና አፈጉባኤ ወይዘሮ ሙሉ ሽመልስ እንደተናገሩት ወንጀሉ የዋግ ሕዝብን የማይወክልና የህዝቡን በሰላም የመኖር ባህል የሚጻረር ነው። በድርጊቱ የተደናገጠው የአካባቢው ህብረተሰብ እንዲረጋጋም አመራሩና የምክር ቤቱ አባላት የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸው ህዝቡ በሰላም ተረጋግቶ ወጥቶ እንዲገባ በስነምግባር ከታነጹት የልዩ ኃይል አባላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም አስረድተዋል። በተፈጠረው ችግር ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች በምክር ቤቱ ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸው ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች መጽናናትን ተመኝተዋል። ትላንት ቀትር ላይ በግለሰቦች መካከል በተነሳ ግጭት ምክንያት በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሶስት የልዩ ኃይሉ አባላት ሲሞቱ ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም