የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ የተጠናከረ ስራ ይጠይቃል- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ - ኢዜአ አማርኛ
የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ የተጠናከረ ስራ ይጠይቃል- ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ
ሰኔ 10/2011 በኢትዮጵያ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ የተጠናከረ ስራ መስራት ተገቢ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። "የውሃና ኢነርጂ ዘርፎች ትራንስፎርሜሽን ለአዲሲቷ የተስፋ አድማስ" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመርሃ-ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በከፍተኛ የለውጥ ጎዳና ላይ የምትገኝ ሲሆን አገሪቱ የሰነቀችውን ተስፋ እውን ለማድረግ ያላትን የውሃና ኢነርጂ ኃብቶች አሟጦ መጠቀም ይገባል። በውሃው ዘርፍ በተለይም የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ አበረታች ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም ወደፊት ብዙ ስራዎች መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር 2015 የተጠናቀቀው የሚሌኒየም የልማት ግቦች ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና ንጽህና አጠባበቅ የተቀመጡ ዕቅዶችን ከሁሉም አገሮች ቀድሞ ማሳካት የቻለች አገር መሆኗን የገለጹት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በአሁኑ ወቅትም የመጠጥ ውሃ እና የንጽህና አጠባበቅን ተደራሽ በማድረግ በኩል ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን ተናግረዋል። ሆኖም በቤተሰብ ደረጃ ዘመናዊ የቧንቧ ውሃ እና የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ አገልግሎት ለማዳረስ ባለድርሻ አካላት ግብ አስቀምጠው ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል። መንግስት ንጹህ የመጠጥ ውሃን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ባለበት ወቅት ንጹህ ውሃ መጠጥ የሚያገኙ ዜጎች አገልግሎቱን የማያገኙ አካባቢዎች ያለውን ችግሮች በመገንዘብ ውሃን በቁጠባና በጥንቃቄ እንዲጠቀሙም አሳስበዋል። ''በአገሪቱ የገጠር ቦታዎች እና በከተሞች የንጽህና አጠባበቅን ለማሻሻል እንዲሁም ምቹ አካባቢን ለመፍጠር በርካታ ስራዎች ከፊታችን ተደቅነው ይገኛሉ'' ብለዋል። በክፍት ቦታዎች እና በሜዳ ላይ መጸዳዳት በማቆምና የቆሻሻ አያያዝና አወጋጋድን በአግባቡ ማከናወን እንደሚገባና ለዚህም በትኩረት መስራት እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ አሳስበዋል። በኢነርጂው ዘርፍም የሚፈለገውን ሃይል ለማግኘት መንግስት የታዳሽ ሃይል አማራጮች መጠቀም ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሬዝዳንቷ በአሁኑ ወቅት 97 በመቶ ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል የምትገኘው ከታዳሽ ሃይል ምንጮች እንደሆነ ጠቁመዋል። የታዳሽ ሃይል ምንጭ አማራጮችን ማስፋት የ2030 የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል። መንግስት በኢነርጂው ዘርፍ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የግሉ ዘርፍ በኢነርጂ ልማት ላይ እንዲሳተፍ የትብብር ማዕቀፍ መዘርጋቱን ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል። ግንባታቸው የተጠናቀቀ እና እየተገነቡ ላሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የኤሌትሪክ ሃይል ለማቅረብ የኤሌትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያዎችና ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመሮችን በመዘርጋት በኩል የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ ይደረጋል ብለዋል። ለኢንዱስትሪ ፓርኮች 1 ሺህ 500 ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ይህን በፍጥነት ተግባራዊ ለማድረግ በቅርቡ ከቻይና የግል ዘርፍ ተቋማት ጋር ስምምነት እንደተደረሰ ጠቁመዋል። በመስኖውም ዘርፍ መንግስት ትኩረት በመስጠት በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አማካኝነት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ዘላቂነት ባለው መልኩ በየዓመቱ እንዲካሄድና ጠቃሚ ነገሮች እንዲገኙበት ከማድረግ አንጻር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጠንካራ ስራ መስራት እንዳለበትም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ አሳስበዋል። የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብቶች ወደተለያዩ ልማቶች በመቀየር የበለጸገችና አዲሲቷ ኢትዮጵያ መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ለማድረግ የተዘጋጀ መርሃ-ግብር ነው ብለዋል። ወጣቱ በውሃና ኢነርጂ ልማት እንዲሁም ጥናትና ምርምሮች ላይ ያለውን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ዓላማ እንደሆነም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሳምንት በዘርፉ የጎንዮሽ ውይይቶች፣ አውደ ርዕዮችና ትዕይንቶች አንደሚካሄዱና ለስትራቴጂዎችና ለፖሊሲዎች የሚሆኑ ምክረ-ሃሳቦች ይገኙበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ ህብረተሰቡን ይበልጥ አሳፊና ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን የዘርፉ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። በመጀመሪያው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሳምንቱን መካሄድ አስመልክቶ የተዘጋጀውን አውድ ርዕይ መርቀው የከፈቱ ሲሆን ከተለያዩ ሚኒስትሮች እና እንግዶች ጋር በመሆን በቦሌ የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ቅጥር ግቢ ችግኝ ተክለዋል። የውሃና ኢነርጂ ሳምንት እስከ ሰኔ 13 ቀን 2011 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከሚደረጉ ውይይቶች በተጨማሪ በሳምንቱ የሚሳተፉት ታዳሚዎች የሚሳተፉበት ቦታ የችግኝ መትከል መርሃ-ግብር እንደተዘጋጀ ለማወቅ ተችሏል። በውይይት መድረኮቹ የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት፣ ሌሎች መንግስታዊ ተቋማት፣ ከዩኒቨርስቲዎችና ከምርምር ማዕከላት የተወጣጡ ምሁራን፣ የግሉ ዘርፍ፣ አጋር ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እና ሌሎች ተቋማት እየተሳተፉ ይገኛሉ።