የአለም ባንክ አለም አቀፍ የልማት ማህበር ስብሰባ ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የአለም ባንክ አለም አቀፍ የልማት ማህበር ስብሰባ ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
ሰኔ 10 / 2011የአለም ባንክ አለም አቀፍ የልማት ማህበር /IDA/ 19ኛ ጉባዔውን ነገ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀምራል። በቀጣዮቹ ሶስት ቀናት የሚካሄደውን ጉባዔ በማስመልከት የዓለም ባንክና የኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስቴር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ጉባዔው የልማት ማህበሩ ላለፉት አመታት ያደረጋቸውን ድጋፎች በመገምገም በቀጣይ በሚያደርጋቸው ድጋፍና ትብብሮች ላይ በማተኮር ይመክራል ተብሏል። በኢትዮጵያ የአለም ባንክ አስተባባሪ ኒኮል ክሊንገ እንደገለጹት በጎባዔው ላይ የመሰረተ ልማት፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ የሴቶች ተሳትፎና ብቃት ማጎልበት፣ የአየር ብክለትና ሌሎችም ጉዳዮች ይነሳሉ። ከድህነት ቅነሳና ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ለአብነትም አገራትን ከድህነት ለማላቀቅ ያላቸው እቅድና ቁርጠኝነት፣ የመፈፀም አቅም ይዳሰሳሉ ብለዋል። የልማት ማህበሩ በአለም ላይ የሚገኙ ታዳጊ አገራትን በማህበራዊና ኢከኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ትብብር በማድረግ በድህነት ቅነሳና መሰረተ ልማት ላይ ትኩረት ያደረገ ድጋፍ ያደርጋል። የአለም ባንክ ዓለም አቀፍ የልማት ማህበር በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያሉ በርካታ የልማት እንቅስቃሴዎችን እየደገፈ መሆኑ ይታወቃል። ማህበሩ እኤአ ከ1991 ጀምሮ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶች 20 ቢሊዮን ዶላር በድጋፍና በብድር መልክ አስተዋጽኦ አድርጓል። ድጋፉ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በድህነት ቅነሳ፣ የሴቶችን ተሳትፎና አቅም በማጎልበትና በእርሻ፣ በትምህርት፣ በጤና እና መሰል ዘርፎች ላይ ያተኮረ ነው። በአለም አቀፍ መስፈርት መሰረት በድህነት ወስጥ የሚገኙ ወይም ታዳጊ አገራት የሚባሉት አገራት ከ1 ሽህ አንድ መቶ ዶላር በታች የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላቸው ሲሆኑ የኢትዮጵያ 883 የአሜሪካን ዶላር መሆኑ የሚታወቅ ነው። የኢፌዲሪ የገንዘብ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ እንደገለጹት፤ ጉባዔው በኢትዮጵያ የሚካሄድበት ዋነኛ ምክንያት አገሪቷ በልማት ማህበሩ ሲደረግላት የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ ባአግባቡ ስራ ላይ በማዋሏ ነው። ኢትዮጵያ በድህነት ቅነሳ፣ በስራ እድል ፈጠራና በሌሎችም ዘርፎች የተሻለች ውጤት አስመዝግባለች ብለዋል። የጉባዔውን መድረክ የዓለም ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ክሪስታሊና ጊዮርጊዮቫ ሲሆኑ ከዚህ ጎን ለጎን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያና በባንኩ መካከል ስላለው ትብብር እንደሚወያዩ ይጠበቃል። በነገው ጉባዔ ከ220 በላይ የለጋሽ አገራት ተወካዮችና ከ30 በላይ የአለም ባንክ አመራሮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።