ቀጥታ፡

የፀረ- ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ትግልን ለማጠናከር የሕዝብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው -ሚኒስትር አዳነች

አክሱም ሰኔ 10 / 2011 የፀረ- ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ ትግልን ለማጠናከር የሕዝብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አመለከቱ። በፌዴራል ጉምሩክ ኮሚሽን የመቀሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የኮንትሮባንድ መከላከል ግብረ ኃይል የመድረክ ውይይት በአክሱም ከተማ አካሄዷል። ሚኒስትሯበዚሁወቅትእንዳስገነዘቡትዜጎችኮንትሮባንድናህገወጥንግድአገርንናሕዝብንእንደሚጎዳበመገንዘብመንግሥትንበቁጥጥሩማገዝይገባቸዋል። ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል ብሎም በኬላ ቁጥጥርና በፀጥታ ኃይል ብቻ ድርጊቱን ማስቆም እንደማይቻልም ገልጸዋል። በየደረጃው ያለው ግብረ ኃይል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ በኃላፊነት ከሰራ ሕዝቡ ተባባሪ ነው ሲሉም ወይዘሮ አዳነች እምነታቸውን ገልጸዋል። የአገሪቱ የወጪ ንግድ እንዲቀዛቀዝና ማህበረሰቡንም ለማናጋት ችግሮች እየተፈጠሩ ያሉት በኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለችግሩ ዋነኛ መፍትሔ የሚሆነው ኮንትሮባንድን የሚጠየፍ ማህብረሰብና አመራር መፍጠር ነው ብለዋል። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ኮንትሮባንድን የሚከላከል ግብረኃይል በአዲስ መልክ ተቋቁሞ ከክልሎች ጋር የሚሰራበት አሰራር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።አሰራሩ ከጸደቀ፤ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ሥራ ላይ እንደሚውል ገልጸዋል። በውይይቱ በፌዴራልና በክልሎች ኮንትሮባንድን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረኃይል ኃላፊነቱን አለመወጣቱ ተገልጿል። በተለይ የጨርቃ ጨርቅ፣ አልባሳትና ኤሌክትሮኒክስ ፣የግብርና ውጤቶችና የማዕድን ህገወጥ ንግድ ትኩረት እንዲሰጠው ተጠይቋል። በተለይ የህገ ወጥ ጦር መሳሪያዎች ዝውውር ሊታሰብበት እንደሚገባ ተመልክቷል። በተጨማሪም የኬላዎች ቁጥጥር ማነስ አገሪቱን የውጭ ንግድ እያሳጣት በመሆኑ እንዲታሰብበትም በውይይቱ ተጠይቋል። ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚኖር ግብይትና ንግድ ግልፅ የሆነ አሰራር ሊኖረው ይገባል የሚሉ ሃሳቦች ተነስተዋል። የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው በጎረቤት አገሮች የሚወጣና የሚገባ ኮንትሮባንድን ለመከላከል በድንበር አካባቢ ግብረ ኃይል በማቋቋም ህጋዊ የጠረፍ ንግድ እንደሚጀመርና ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውርን ለመግታት የቁጥጥር ሥርዓቱን እናጠናክራለን ብለዋል። ከኤርትራ ጋር ባለው መሥመር በራማና በዛላ አንበሳ ኬላዎች እንደተከፈቱና በቅርቡ ደግሞ በሁመራ ኬላ ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በአገሮቹ መካከል ያለው ንግድ ሕጋዊ አሰራርን ተከትሎ እንዲቀጥል በመሰራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። ባለፉት አምስት አመታት 4ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም