ቀጥታ፡

በመንግስት የተወሰደው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ፋይዳው የጎላ ነው...የራያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

ማይጨው ሰኔ 1/10/2010 የኢህኤዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመንግስት ስር የሚገኙ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ድርሻ ወደግል ለማስተላለፍ ያሳለፈው ውሳኔ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የራያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ፡፡ ኮሚቴው በቅርቡ ባካሄደው ስብሰባ በመንግስት ስር የሚገኙ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች ሙሉ በመሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ድርሻ ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች አንዲተላለፉ ወስኗል፡፡ በራያ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ነጋ አፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት በመንግስት የተወሰደው የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ  እየተመዘገበ የመጣው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይ እንዲሆን ያደርጋል። በተለይ አገሪቱ ተጨማሪ የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ የጀመረችው የዕድገት ጉዞ  እንዲፋጠን የሚያደርግ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ በግል ባለሀብቶች የሚፈጠረው የሽርክና ሥራ በውድድር ላይ የተመሰረተ የገበያና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለመፍጠር እንደሚያስችል ዶክተር ነጋ አመልክተዋል፡፡ የገበያ ክፍተት ባለባቸው ጉዳዮች  የመንግስት የልማት ተዋናይነትን ማሳደግና ክፍተቱ ሲሸፈን ባላሃብቶች በአክሲዎን ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግ የልማታዊ መንግስት ባህሪ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ "ሥራ አስፈጻሚው የወሰደው የኢኮኖሚ መሻሻያ እርምጃ በሀገሪቱ የሚታየውን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ከማጠናከር ባለፈ በመንግስት ያልተሸፈኑ የህዝብ ፍላጎትችን ለሟሟላት ይረዳል" ብለዋል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ በውድድር ላይ የተገነባ ጥራቱን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ነው ዶክተር ነጋ የገለጹት። በተለይ ባለሀብቶች ይዘውት የሚመጡት ቴክኖሎጂና ሀብት ሀገሪቱ የምትከተለው ኢንዱስትሪ መር የልማት ስትራቴጂ እውን እንዲሆን የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው የኢኮኖሚ ምሁሩ አመልክተዋል፡፡ እንደእርሳቸው ገለጻ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ በእስያ ሀገራትም ጭምር በስፋት እየተተገበረ መጥቷል፡፡ በህንድ አገር በቴሌኮም ልማት የተሰማሩ ኩባንያዎች በዋጋው ቅናሽ ብቻ ሳይሆን ጥራቱ የተጠበቀ የቴሌኮም አገልግሎትን በማስፋፋት ተጠቃሚ መሆናቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ዶክተር ነጋ እንዳሉት የአክሲዮን ደርሻ ኢኮኖሚውን አቅጣጫ ስቶ አገሪቱን እንዳይጎዳ የመንግስት ድርሻን ጠብቆ ለማቆየት የጥንቃቄ እርምጃዎችን በየጊዜው መውስድ ተገቢ ነው፡፡ አገሪቱ የምትመራበትን የኢንዱስትሪ መሪ የልማት ስትራቴጂ  ለመተግበር በወሳኝ የልማት ድርጅቶች ውስጥ የባለሃብቶች ተሳትፎን መፍቀድ ወቅቱን የጠበቀ ውሳኔ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ ትምህርት መምህር ገብሩሊባኖስ ሀዱሽ ናቸው፡፡ የህዝቦችን የመሰረተ ልማት ፍላጎት ለማረጋገጥ መንግስት እንደ ኤሌክትሪክና ቴሌኮም ያሉ ወሳኝ የልማት ድርጅቶችን በብችነት በማስተዳደር ላለፉት ዓመታት ያከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ አሁን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ያስተላለፈው ውሳኔ በአገሪቱ እያጋጠሙ ያሉትን  የእድገት ማነቆዎች የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል። ከእዚህ በተጨማሪ የተሻለ  የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት፣ ቴክኖሎጂን ለማስመጣት፣ ለዜጎች አማራጭ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ጎን ለጎንም የኑሮ ውድነት ችግርን ለመቀነስ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት። "ጥራቱን የጠበቀ  ምርት በአይነትና በብዛት ወደ ሕብረተሰብ ለማቅረብ ይረዳል" ያሉት መምህር ገብሩሊባኖስ ውሳኔው ከልማታዊ መንግስት ጽንስ ሀሳብ የሚቃረን አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉና በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ ያሉ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴል እና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንደሚተላለፉ መወሰኑ ይታወሳል። በተጨማሪም የኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክሲዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች በአክሲዮን ድርሻ እንዲተላለፉ የሚደረግ መሆኑም እንዲሁ። ይህም በአገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ፈጣን እድገት ዜጎችን አካታች በሆነ መልኩ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የሚያደርግ መሆኑ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም