ቀጥታ፡

የሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ ዓመታዊ የማራቶን ውድድር በባህር ዳር ተካሄደ

ባህር ዳር ሰኔ 9/2011 ከአንድ ሺህ የሚበልጡ አትሌቶች የተሳተፉበት 35ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ ዓመታዊ የማራቶን ውድድር ዛሬ በባህር ዳር ተካሄደ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ውድድር መነሻና መድረሻውን የቀድሞው ግዮን ሆቴል አድርጎ ነበር። በወንዶች በተደረገው ውድድር አንደኛ ፍቅር በቀለ ከፌዴራል ፖሊስ ፣ ሁለተኛ መኳንንት አየነው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ሦስተኛ ብርዬ ተሾመ ከፌዴራል ፖሊስ ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል። አትሌት ፍቅር ''በ42 ኪሎ ሜትር የወንዶች ማራቶን አንደኛ ሆኜ በማጠናቀቄ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል'' ብሏል። በርቀቱ አንደኛ ሲወጣም ለመጀመሪያ ጊዜው እንደሆነም ተናግሯል። በሴቶች ተመሳሳይ ርቀት አሸቴ በከሬ ከኦሮሚያ ፖሊስ ፣ ዘይቱን አረቦ ከፌዴራል ማረሚያ ፣ መሰረት ድንቄ በግል የመጀመሪያዎቹን ሦስት ደረጃዎች በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋ። አትሌት አሸቴ ''በውቢቷ ባህርዳር ከተማ አሸናፊ ሆኜ የወርቅ ሜዳሊያ ለክለቤ ማምጣቴ ከልብ አስደስቶኛል'' ብላለች። በተለይ በክልሎች የሚካሄዱ ውድድሮች ታዳጊዎች እንዲበረታቱ ከማድረግ ባለፈ፤ ተተኪ አትሌቶች በየአካባቢው በብዛት እንዲወጡ እድል ይሰጣል ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች። እንዲሁም በአንጋፋ አዋቂ አትሌቶች ከ50 ዓመት በታች በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ውድድር ገዛኸኝ ገብሬ፣ በሪሁን ተስፋዬና  ቶሎሳ ገብሬ  አሸናፊዎች ሆነዋል። ከሃምሳ ዓመት በላይ የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ አያሌው እንዳለ ፣ይበልጣል ቢያልፈውና ተስፋዬ ጉታ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ወጥተዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ዓመታዊው  የሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ ውድድር በክልሎች መካሄዱ ስፖርቱን ለማስፋፋት ያግዛል። እንዲሁም አቅም ያላቸው ተተኪ አትሌቶች ለማውጣት ያስችላል ብለዋል። የባህርዳርና የአካባቢው ነዋሪዎች ውድድሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ያደረጉት አስተዋጽኦና ጨዋነትን ለተላበሰ መስተንግዶ ፕሬዚዳንቷ ምስጋና አቅርበዋል። ውድድሩን ያስጀመሩት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳውና ሌሎች እንግዶች ነበሩ። በውድድሩ እስከ 10ኛ ለወጡ የገንዘብ፣ የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ለውድድሩ ስኬት አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም