በ5 ነጥብ 2 በሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የድሬዳዋ ደወሌ የክፍያ መንገድ ተመረቀ

169
ሰኔ 9/2011 5 ነጥብ 2 በሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የድሬዳዋ ደወሌ የክፍያ መንገድ ዛሬ በይፋ ተመርቆ ወደስራ ገብቷል። በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 220 ኪሎሜትር  ርቀት የሚሸፍነው ይህ መንገድ ከአዲስ አበባ-አዳማ የፍጥነት መንገድ በመቀጠል ሁለተኛው የክፍያ መንገድ ነው። የግንባታው ወጪ 85 በመቶ ከቻይና ኤግዚም ባንክ የተገኘ ብድርና ቀሪው 15 በመቶ በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ነው። የድሬዳዋ-ደወሌ መንገድ የቀድሞ ገጽታ በጠጠር የመንገድ ደረጃ የነበረ ሲሆን ይህም በተለያያ ጊዜያት የጎርፍና የመሬት መናድ አደጋ እያጋጠመው የትራፊክ ፍሰትን ከማስተጎጎል ባሻገር ተሽከርካሪዎችን ለተደጋጋሚ ብልሽት ይዳርግ እንደነበር ተገልጿል። በመንገድ ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የትራንስፖርት ሚንስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንዳገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ፕሮጀክቶችን በቅርበት በመከታተልና በመደገፍ ላይ ነው። የዚህ መንገድ መገንባት ሊያበረክተው ከሚችለው ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ባሻገር መንገዱ በጠጠር መንገድ ደረጃ እያለ ይወስድ የነበረውን የ10 ሰዓት ጉዞ ወደ 4 ሰዓት ዝቅ ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል። በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ አገልግሎት ላይ የሚገኘው የአዳማ አዋሽ ጋላዲ መንገድ ላይ ይደርስ የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ የሚያቃልል መሆኑን ጠቁመዋል። መንገዱ የጎረቤት አገር ከሆነችው የጅቡቲ ወደብ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ የሁለቱን አገሮች የንግድና የህዝብ ለህዝብ ትስስር የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑም ተገልጿል። በ2007 ዓ.ም በቻይናው ሲጂሲ ኩባንያ የተጀመረው የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ በ4 ዓመታት ውስጥ ተጠናቋል ተብሏል፡፡ በመንገዱ ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ መሀመድ የመገንዱ መገንባት የታለመለትን ዓላማ ለማሳካት የአካባቢው ህብረተሰብ ሰላሙን መጠበቅ እንዳለበት አስረድተዋል። የትራንስፖርት ሚኒስትሯና የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር መንገዱን ከመረቁ በኋላ ክፍያ በመፈጸም በመንገዱ ተጉዘዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም