ቀጥታ፡

በከተማው ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ችግኝ ይተከላል- የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ

ሰኔ9/2011 በከተማው ሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ቀጣይ ማክስኞ እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡ ትምህርት ቤቶች በአረንጓዴ መሸፈናቸው የመማር ማስተማር ሥራ  ምቹ እንዲሆን በማድረግ የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥም  ሚናው የጎላ እንደሆነ ተገልጿል።   የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት እንደተናገሩት፤ የከተማው ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በተገኙበት በዳግማዊ ሚኒሊክና በየካቲት አስራ ሁለት ትምህርት ቤቶች የክረምት ችግኝ ተከላ ፕሮግራም ባለፈው ሳምንት  ተጀምሯል፡፡ በሁለቱ ትምህርት ቤቶች የተጀመረው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በሌሎችም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ሰኔ 11/2011 ዓ.ም እንደሚከናወን ተናግረዋል። በተለይ በአረንጓዴ ባልተሸፈኑ ትምህርት ቤቶች ላይ የችግኝ ተከላው በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚከናወን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ችግኞቹ  እስኪያድጉ ድረስ  በተማሪው ና በትምህርት ማህበረሰቡ እንክብካቤ ይደረግለታል ብለዋል። ተማሪዎች ስለ አከባቢ ጥበቃ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ከመደበኛትምህርት በተጨማሪ ከከተማው አካባቢ ጥበቃ ጋር በመሆን በአረንጓዴ ልማት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ  በቀጣይም  በተከታታይ ይሰራል ብለዋል።    የቀለመ ወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ኤሊያስ ግደይ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ከሁለት መቶ በላይ ችግኞች ተማሪዎችን ና የትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ በማሳተፍ በዚህ ሳምንት መተከሉን ተናግረዋል፡፡ የተተከሉት ችግኞች አድገው የትምህርት ቤቱን አረንጓዴ ሽፋን እንዲጨምር ከባለሙያዎች እገዛ  በተጨማሪ ችግኞቹን ለተማሪዎች በመስጠት እንዲከባከቡ ይደረጋል ብለዋል። ትምህርት ቤቱ ለአረንጓዴ አካባቢ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ውጤታማ መሆኑን የተናገሩት  ርዕሰ መምህሩ፤ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በጥሩ መንፈስ እንዲከታተሉና እንዲያጠኑ እያደረጋቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ዛፎች ትምህርት ቤቶችን መማር ማስተማርን ምቹ በማድረግ፣ ንጹህ አየር እንዲተነፍሱ ና  ደስተኛ እንዲሆኑ ስለሚያደርግ  በትምህርት ቤቶቹ  ችግኞች መተከላቸው  ጠቃሚ መሆኑን የተናገረችው የሚኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ  ሰላማዊት ታደሰ ናት፡፡ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የቤተሰብ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ችግኞችም እንዲያድጉ እንክብካቤ ስለሚያስፈልጋቸው ሃላፊነቷን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች። በአዲስ አበባ ከተማ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃና ልማት ኮሚሽን  መረጃ ያሳያል።   
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም