ከመንግስት ወደ ግል በሚተላለፉ የአክስዮን ድርሻዎች ላይ የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የቁጥጥር ስራዎች ይቀጥላሉ- የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ከመንግስት ወደ ግል በሚተላለፉ የአክስዮን ድርሻዎች ላይ የህዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የቁጥጥር ስራዎች ይቀጥላሉ- የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2010 በኢኮኖሚ ማሻሻያው በከፊልም ሆነ በሙሉ ከመንግስት ወደ ግል በሚተላለፉ የልማት ድርጅቶች አክስዮን ድርሻዎች ላይ የልማቱን ቀጣይነትና ፍትሃዊ ውድድሩን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አስፈላጊ የቁጥጥር ስራዎች በመንግስት በኩል እንደሚደረጉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የኢኮኖሚ ማሻሻያው መንግስት እስካሁን ይከተለው የነበረውን የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መሰረት አድርጎ የሚተገበር መሆኑም ተገልጿል። ማሻሻያው አገሪቱ አሁን ካለችበት ኢኮኖሚያዊ እድገት አንፃር የሚገጥሙ ማነቆዎችን የሚፈታና በቂ ጥናት የተደረገበት እንደሆነ ታውቋል። የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አገሪቱ ላለፉት አመታት የነበረችበትን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታ የገመገመ ሲሆን በመንግስት ይዞታ ስር ያሉ የልማት ድርጅቶች በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ባለሃብቶች እንዲተላለፉ መወሰኑ ይታወቃል። ከነዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይልና የኢትዮጵያ ትራንዚትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅቶች በዋናነት በመንግስት ስር ሆነው በከፊል የግሉ ዘርፍ የአክስዮን ድርሻ እንዲኖረው ይደረጋል። እንደ ባቡር፣ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ስኳር ኮርፖሬሽንና መሰል የልማት ድርጅቶች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ የሚተላለፉ ይሆናል። በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ በአክሲዮን በሚተላለፉ የልማት ድርጅቶች ላይ መንግስት የቁጥጥር ስራውን እንደሚሰራ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ዕህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። የኢኮኖሚ ማሻሻያው የልማታዊ መንግስት ስርዓትን ከሚከተሉ እንደ ቻይናና ኮሪያ ልምድ የተቀመረበትና አዋጭ መሆኑ የታመነበት መሆኑንም ተናግረዋል። 'የግል ባለሃብቱን ተሳትፎ በማስፋት ረገድ እስካሁን ብዙ አልሄድንም ነበር' ያሉት ሚኒስትሩ የአገሪቱን የፋይናንስ አቅም ለማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬን ለማምጣት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋትና መሰረተ ልማት ግንባታን ለማፋጠን ርምጃው ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል። የኢኮኖሚ እድገቱን ተከትሎ ያጋጥሙ የነበሩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚፈታና የግል ባለሃብቶችን አቅምና ተሳትፎ በማሳደግ ልማታዊ ስርዓቱን የበለጠ የሚያሳድግና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ጠቁመዋል። በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በትርፋማነቱና ኢትዮጵያን ከሌላው አለም ጋር በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንደነበረው ያወሱት ሚኒስትሩ በቀጣይም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ የአገሪቱ መለያ ቀለም እንደሆነ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ ም ባካሄደው ጉባዔ 'በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉ በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴል እና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ፣ እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል።