”ቦሌ የጠፋው ገንዘብ ከ2 ዓመት በኋላ ሾላ ተገኘ ”

116
ገብረህይወት ካህሳይ ከኢዜአ ነገሩ የሆነውቦሌ ክፍለ ከተማ ሰንሻይን አካባቢ ይገኝ በነበረ አንድ ትልቅ የመንግስት ተቋም ውስጥ ነው ። ተቋሙ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ይባል ነበር ። የተቋሙ ሠራተኛ ለአንድ የተቀደሰ ዓላማ ከወርሃዊ ደመወዟ አጠራቅማ ያስቀመጠችው ጥሬ ገንዘብ ባልታወቀ ምክንያት ከተቆለፈው የሳጥን መሳቢዋ ታጠዋለች ። ወቅቱ ታህሳስ ወር 2009 ዓ.ም ነበር ። ”ቦሌ” የጠፋው ገንዘብ ከሁለት ዓመት ከአምስት ወር  በኋላ ” ሾላ ” መገኘቱ ትኩረቴን ሳበውና አጋጣሚውን ላጋራችሁ ወደድኩኝ ። ሠራተኛዋ ምስራቅ  ስንሻው ትባላለች ። ገንዘቡ ያስቀመጠችበት ቦታ ላይ ደግማ ደጋግማ ብትፈትሽም ልታገኘው አልቻለችም ። ሌሎችን ከመጠርጠር ይልቅ እራሷን ተጠያቂ ማድረጉን አስቀደመችና ፍለጋዋን ወደ መኖሪያ ቤቷ ጭምር አደረገች ። ይሁን እንጂ መንም የለም። በዘመኑ አባባል ወፍ የለም እንደሚባለው ። ቀናት ሳምንታትን ፣ ሳምንታት ወራትን እያስከተሉ ነጎዱ ። እሷም ፍለጋውን እርግፍ አድርጋ ተወችው ። በሒደት ደግሞ ከነአካቴው ረሳችው ። የጊዜ ሒደት እራሱ አዲስ ሒደት ይዞ ብቅ አለ ። የማይነካ ይመስል የነበረው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮችም ፈረሰ ። በተቋሙ የነበሩ ሰራተኞች ወደ ተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተበትነው ተመደቡ ። በዚያ ልክ የተቋሙ ንብረት ሰራተኞቹን  ለተቀበሉ መስሪያ ቤቶች እንዲከፋፈል ተወሰነ ። ከቀድሞ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት የተወሰኑ ሰራተኞች ከተረከቡ ተቋማት መካከል ደግሞ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ አንዱ ነው ። ኢዜአ ከ60 በላይ ሰራተኞች ተቀብሏል ። የድርሻውን ንብረትም ወስዷል። ኢዜአ ከተረከባቸው ንብረቶች መካከል የማይጠቀምባቸውን በጨረታ ሽያጭ እንዲወገዱ ይወስናል ። ጨረታው ተከፍቶ አሸናፊዎች ተለዩና ዕቃው የሚጫንበት ጊዜ ደረሰ ። አብዛኛዎቹ የተሸጡ ዕቃዎች የእንጨት ውጤቶች ነበሩ ። ከሚጫኑት ዕቃዎች መካከል አንዲትመሳቢያዎች ያላትሳጥንነገር  የአንዱን ሰው ቀልብ ሳበች ። የትኩረቱ ምክንያት ደግሞ ቁልፍ ያላቸው ሦስትተካፋች መያዟንና ውብ መሆኗ ነበር ። በሌላ ተመሳሳይ ዕቃ እንዲቀየርለት የጨረታውን አሸናፊ በማስፈቀድ ዕቃዋን ከመጫን አስቀራት ። ሰውየው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ንብረት ክፍል ባልደረባ አቶ ገብረስላሴ በሻዳ ይባላሉ። የወደዱቱንባለመሳቢያ  /Drawer/   ማፀዳዳት ጀመሩና  አንደኛና ሁለተኛውን ተካፋች ቁልፉ በትክክል እንደሚሰሩ አረጋገጡ ። ሦስተኛው ተካፋች ግን በአግባቡ አልታዘዝ አለ ። ተቀርቅሮ አላዘጋ አላስከፍት ያለ ባዕድ ነገር እንዳይኖር ተጠራጥረው በደንብ መፈተሽ ጀመሩ ። ድንገትከመሳቢያው ስር ተቋጥሮ የተንጠለጠለ ፌስታል ተገኘ። አቶ ገብረስላሴ ፌስታሉን በብልሃት አውጥተው ከፈቱ ። ያጋጠማቸው ግን ያልተጠበቀ ነገር ነበር ። 3 ሺህ 700 ብር የወረቀት  ገንዘብ ፣ የተወሰኑ የብረት ሳንቲሞች ፣ የወይዘሮ ምስራቅ ስንሻው ፎቶ ግራፍ  የተለጠፈበት  የባንክ ደብተርና ኤ ቲ ኤም ሆኖ ተገኘ ። አቶ ገብረስላሴ ገንዘቡ አላታለላቸውም ። የወይዘሮ ምስራቅን ስልክ አፈላልገው መደወልን ምርጫቸው አደረጉ - ለእምነታቸው የፀኑ ታማኝ ሰው ። ስልክ ደውለው ” የጠፋብሽ ንብረት አለ? ” ሲሉ  ጠየቋት ። ወይዘሮ ምስራቅ ጊዜው ከመርዘሙ የተነሳ ረስታው ነበርና ” ኧረ በፍፁም ” የሚል መልስ ትሰጣለች። ” ኧረ ፎቶ ግራፍሽ ያለበት የባንክ ደብተርና ኤ ቲ ኤም ጭምር ያካተተ ንብረት ነው ” ብሎ ፍንጭ ሲሰጧት ” አዎን! ጠፍቶብኛል ። ለስለት ከወርሃዊ ደመወዜ ያጠራቀምኩት ገንዘብ አብሮ ጠፍቶብኛል ” በማለት በምልክት ማስረጃዎች እውነታውን ታረጋግጠለታለች ። ወይዘሮ ምስራቅ ቦሌ የጠፋውን ንብረትዋን ከሁለት ዓመት ከአምስት ወር በኋላ ሾላ በሚገኘው ኢዜአ (የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት) ግቢ ውስጥ ታገኘዋለች። እንባ እየተናነቃት የሀቅ ገንዘቧን እንዲገኝ ለረዳት ፈጣሪዋ ምክንያት ሆኖ ታማኝነቱን ላረጋገጠላት አቶ ገብረስላሴ ምስጋናዋን አቀረበች ። ገጠመኙን የሰማው ሁሉ ተደንቋል ። በተለይ የአቶ ገብረስላሴ ታማኝነት የሚገርም ብቻ ሳይሆን አስደናቂም ጭምር ነበር ። አቶ ገብረስላሴ ” የሰው ነገር የሰው ነውና ለባለቤቷ መመለሴ አዲስ ነገር የለውም ” ሲል ቀለል አድርጎ ቢያቀርበውም ለበርካቶቻችን ግን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ። በሆነ አጋጣሚ በአጅ የገባውን ገንዘብ ቀርቶ ከምንሰራባቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ቁራቁምቦውን ሳይቀር የምናግበሰብስ ስንቶቻችን ነን ። ከምንሰራበት ኮምፕዩተር ማውዝ ነቅለን ደብቀን የወሰድን ጥቂት ስግብግቦች በያለንበት ከዚህ ገጠመኝ ምን እንማራለን ? መልሱ ከእኛው ለእኛው ልተወው ። አቶ ገብረስላሴ አሁን ላሳዩት ታማኝነት አክብሮት ፣ እውቅናና ሽልማት ያስፈልጋቸዋል ። ለረጅም ዓመታት ካገለገሉበት ኢዜአ በመጪው ታህሳስ ወር በጡረታ የሚገለሉት "አቶ ገብሬ" ለወጣቶች መልካም አርአያነታቸውን በተግባር በማሳየታቸው አድናቆቴን እገልጽላቸዋለሁ ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም